የኮቪድ-19 መመርመሪያ ማሽን ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነ

በአጠቃቀሙ ዙሪያ ለጤና ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጥቷል ዲዩ፤ መስከረም 28 ቀን 2013 ዓ/ም፣ (ሕ.ግ) ዲላ ዩኒቨርሲቲ ያስመጣው የኮቪድ-19 መመርመሪያ ማሽን በጥቅምት ወር አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ዶ/ር ፍራኦል ንፍታሌም የተግባር ስልጠና እና ትምህርት ዋና ዳይሬክተር እና የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅና በሪፈራል ሆስፒታል ም/ፕሬዚዳንት ተወካይ ገለጹ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ጊዜያት ለኮቪድ-19 ምርመራ ከጌዴኦ ዞን ናሙና ወደ ሀዋሳ ይላክ የነበረውን ለማስቀረት መመርመሪያ ማሽን መግዛቱን አስታውሰው በሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ አገልግሎት ለመስጠት የጤና ባለሙያዎችን ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንቲትዩት በመጡ ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን ዶ/ር ፍራኦል አስታወቀዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ኢንቲትዩት የመጡት የላብራቶሪ ባለሙያና አሰልጣኝ አቶ ነጋሳ አመኑ የኮቪድ-19 ማሽን (PCR) ምርመራ ላቦራቶሪ ለሁለት ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን ገልጸው ማሽኑ በአንድ ጊዜ 96 ናሙና (sample run) ማድረግ እንደሚችልና 96 ናሙና 3ቱን የጥራት ቁጥጥር በትክክል መስራቱንና አለመስራቱን የሚልጽ በመሆኑ 93 ናሙና በሁለት ሰዓት ውስጥ ሰለሚሠራ በቀን ውስጥ ምን ያህል መስራት እንደሚቻል ለማውቅ ስልጠና እንደሰጡ እና በ24 ሰዓት ውስጥ እስከ 500 ናሙና መስራት እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡ ሰልጣኞች የሰለጠኑትን በተግባር ጭምር መስራት እንደቻሉ አሰልጣኙ ተናግረዋል፡፡ የማይክሮ ባዮሎጂ ባለሙያ የሆኑት መምህር ኩማ ድርባ ከዚህ በፊት በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጸው ከመስከረም 25/2013 ዓ/ም ጀምሮ ለ3 ቀን የወሰዱት ስልጠና በቂና የሚያሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሌላው ሰልጣኝ መምህር አሸናፊ ተስፋዬ በበኩላቸው ከዚህ በኋላ ብቻቸውን በማሽኑ መስራት እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ፍራኦል የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅና ሪፈራል ሆስፒታል ባለሙያዎችን በተለይም የላብራቶሪ ባለሙያዎችን አመስግነዋል፡፡