የአባያ-ጫሞ ንዑስ ተፋሰስ ጥናት ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ''ዎርክሾፕ'' ተካሄደ

ዲ.ዩ፦ ግንቦት 19/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ከቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተፋሰስ አስተዳደር ፅ/ቤት በጋራ ትብብር የሚያከናውኑትን የውሃ ጥናት "ABAYA - CHAMO SUB-BASIN WATER ALLOCATION PLANNING" የማስጀመሪያ "ዎርክሾፕ" በዛሬው እለት በዲላ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።
በፕሮግራሙ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት ደረጀ ክፍሌ (ዶ/ር)፣ የጥናት ቡድኑ አባል፤ ባለፉት አራት አመታት የስምጥ ሸለቆ ተፋሰስን ትኩረት ያደረገ፤ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመቀናጀት በርካታ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አንስተዋል።
አያይዘውም፤ የተጀመረውን ስራ በአግባቡ መሬት ላይ ለማውረድና ስራውን ለማቅለል የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ በክላስተር ተለይቶ አባያ- ጫሞ የስምጥ ሸለቆ ክፍል ዲላ ዩኒቨርሲቲ እና ቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ አስተዳደር ፅ/ቤት በጋራ በመሆን ቅደመ ዝግጀት አጠናቀው ዛሬ የማስጀመሪያ "ዎርክሾፕ" ለማከናወን መብቃቱን ገልፀዋል።
ዶ/ር ደረጀ አክለውም፤ ፕሮጀክቱ የሁላችንም በመሆኑ የበኩላችንን በጀት በመመደብ፣ የአመራር ክትትልና ቁጥጥር ስርዓት በመዘርጋት በተያዘለት መርሐግብር እንዲጠናቀቅ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
አቶ ደቢሶ ደደ፣ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ አስተዳደር ፅ/ቤት ሀላፊ፤ በበኩላቸው መስሪያ ቤታቸው በተሰጠው ስልጣን መሰረት በስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተፋሰስ ያለውን የውሀ ሀብት ለሀገር ልማትና ብልፅግና እንዲውል ምቹ ሁኔታ መፍጠር ከተልዕኮው አንዱ ነው ብለዋል። ይህን ተልዕኮ ለማሳካትም ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በአጋርነት ለሀገርና ህዝብ የሚጠቅም ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም መሰረት በክላስተር በመለየት ሀዋሳ፣ ዝዋይ-ሻላ፣ ጨው ባህር፣ አባያ-ጫሞ ተፋሰስና ሌሎች ጥናትና ምርምር በማካሄድ ተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማስፈን ያለመ ስራ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።
ፍቃዱ ወልደማርያም (ዶ/ር)፣ የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትና የጥናት ቡድኑ አባል፣ የፕሮጀክቱን የመነሻ ፅሑፍ ለመድረኩ ታዳሚዎች ገለፃ አድርገዋል።
በቀረበው ጽሑፍ ላይ ከምሁራንና ባለሙያዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና ሀሳቦች ተነስው፤ ወይይቱን የመሩት ዶ/ር ፍቃዱ ወልደማርያም እና አቶ ደቢሶ ደደ መልስና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ በተጨማሪ በመድረኩ የተነሱ ጠቃሚ ሀሳቦችን እንደ ግብዓት እንደሚጠቀሙባቸው ገልጸዋል።
በመርሐግብሩ የዲላ ዩኒቨርሲቲ እና ቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተፋሰስ ፕላን ዴስክ ሀላፊ አቶ ተከተል ታደሰ፣ የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተፋሰስ አስተዳደር ፅ/ቤት ሀላፊ እና ባለሙያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ