ዲ.ዩ፤ መጋቢት 14/2016 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የዲላ ዩኒቨርሲቲ በሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን “ሴቶችን እናብቃ፣ ልማትና ሰላምን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ሃሳብ ከዩኒቨርሲቲው አንጋፋ ሴት መምህራን ጋር የልምድ ልውውጥ በማድረግ በዓሉን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች አክብሮ ውሏል። ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ113ኛ ጊዜ እንዲሁም በሀገራችን ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ ተከብሮ መዋሉ ታውቋል።
በዓሉን በንግግር የከፈቱት ጦይባ ሻፊ (ዶ/ር)፣ የአካዳሚክ ፕሮግራም የመማር ማስተማር ምክትል ዳይሬክተር፤ “በዩኒቨርሲቲው የምትገኙ ራሳችሁን በትምህርት ያበለፀጋችሁ ዶክተሮች፣ ጥሪ የተደረገላችሁ ሴት መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞች እና ተማሪዎች እንኳን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ113ኛ በአገራችን ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ እየተከበረ ለሚገኘው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን እንኳን አደረሳችሁ” በማለት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዶ/ር ጦይባ አክለውም፤ ይህ በዓል የሚከበረው ኢትዮጵያ ሴቶችን በሚመለከት የፈረመቻቸውን አገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በማሰብ እንደሆነ ገልጸው፤ ከዛ ባለፈ ግን በዓሉ ሴቶች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን አብሮነት በማጠናከር የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ቃላቸውን የሚያድሱበት እንደሆነ ተናግረዋል።
ወ/ሮ አለሚቱ ብርሃኑ፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክተር በበኩላቸው፤ ይህ መድረክ የተዘጋጀው በአለም አቀፍ ደረጃ ጭምር በአንድነት የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ከማሳብ ባለፈ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ አንጋፋ ሴት መምህራንን፤ ለጀማሪ ሴት መምህራን ልምዳቸውን እና ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉ በማስብ እንደሆነ ገልጸዋል።
በፕሮግራሙ በዩኒቨርሲቲው ስኬታማና ውጤታማ ተምሳሌት መምህራን በመሆን ዶ/ር ጦይባ ሻፊ፣ ዶ/ር አባይነሽ ክንዴ እና ዶ/ር ኮከብ አያሌው፤ በበዓሉ ላይ ለተገኙ መምህራን የሕይወት ልምዳቸውንና ተሞክሯቸውን አካፍለዋል።
በተለይም ዶ/ር ጦይባ ሻፊ፣ በዕለቱ በትምህርት ቆይታቸው ወቅት ያሳለፉትን ውጣ ውረድ ያቀረቡበት ሁኔታ ለብዙ ሴት መምህራን ስለ ጽናት እና ጥንካሬ ትልቅ ልምድ ያስጨበጠ ነበር።
በዩኒቨርሲቲው የሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ የሥርዓተ ፆታ አስተባባሪ እና የሴት መምህራን ኔትዎርክ ተጠሪ የሆኑት መምህርት አይናዲስ አንተነህ፤ በዩኒቨርሲቲው የሴት መምህራን ፎረም ዋና ተግባራትን በተመለከተ በመድረኩ ገለፃ ሰጥተዋል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ፤
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
Facebook:
https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://www.t.me
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et