ዲ.ዩ፤ ጥር 10/2016 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የጤናና ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ አጠቃላይ ሆስፒታል የሕክምና እና አንስቴዥያ ተመራቂ ተማሪዎች በይርጋጨፌ ከተማ የተለያዩ ችግር ፈቺ ፕሮጀክቶችን ሰርተው ማስመረቃቸው ተገልጿል።
አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የጤናና ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ አጠቃላይ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንደገለጹት፤ የሕክምና እና አንስቴዥያ እጩ ተመራቂ ተማሪዎች በይርጋ ጨፌ ከተማ በቡድን ስልጠና መርሐ ግብር (TTP) ወጥተው ባሳለፏቸው አራት ሳምንታት የማህበረሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ጤና ነክ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት የሕዝብ መፀዳጃ ቤት ግንባታ፣ በይርጋጨፌ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የአዕምሮ ጤናና ስነ-ተዋልዶ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እንዲሁም ተላላፊ በሽታዎችን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎችን መስራታቸውን ገልጸዋል።
በፕሮጀክቶቹ ምረቃ ወቅት የተገኙት አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ ለነዚህ ፕሮጀክቶች መሳካት ከተማሪዎች ጎን የነበሩትን መምህራን እንዲሁም ‘HEPI’ (Health Professionals Education Partnership) ፕሮጀክት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አመስግነዋል።
አቶ ትግሉ ኃይሉ፣ በይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት የእናቶችና ሕፃናት ጤና ሥራ ሂደት አስተባባሪ በበኩላቸው፤ የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት ለከተማው ትልቅ እድል መሆኑን ገልጸው፤ ይህንን ፕሮጀክት ቀርጸው ለሰሩ ተማሪዎችና መምህራን እንዲሁም ለሌሎች ተሳታፊ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በቡድን ስልጠና መርሐ ግብሩ (TTP) ከተሳተፉ ተማሪዎች መካከል በዲላ ዩኒቨርሲቲ የጤናና ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ አጠቃላይ ሆስፒታል የህክምና ተማሪ እጩ ዶክተር አቤንኤዘር በለጠ፤ በአካባቢው ጤና ነክ ተብለው የተለዩ ችግሮችን መሰረት በማድረግ ፕሮጀክቶችን መስራታቸውን ገልጾልናል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት