ዲ.ዩ፤ የካቲት 17/2016 ዓ/ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማሕበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት በዲላ ከተማ ለሚገኙ አካል ጉዳተኛ ማሕበራት አባላት በፕሮጀክት ዕቅድ አዘገጃጀት ዙርያ ስልጠና ተሰጥቷል።
አባቡ ተሾመ (ዶ/ር)፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጋፍ ማዕከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ አካል ጉዳተኝነት በተፈጥሮ፣ በሰው ሰራሽ አደጋ፣ በየትኛውም ሰዓት በሁሉም ሰው ላይ ሊከሰት እንደሚችል ጠቁመው፤ ለአካል ጉዳተኞች አካታች የትምህርት ስርዓትና የስራ ዕድል መፍጠር ለአካል ጉዳተኛው ብቻ ሳይሆን ለአካባቢውና ለአገር እድገት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት ሰጥቶ እያደረገ ያለው እገዛና ድጋፍ የሚበረታታና ለቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ዶ/ር አባቡ አስገንዝበዋል።
አቶ ተካልኝ ታደሰ፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማሕበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በበኩላቸው፤ ስልጠናው ነአካል ጉዳተኞችን እውቀትና ክህሎት ማሳደግን ዓላማ ያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ አካል ጉዳተኞች ለራሳቸው ብሎም ለማሕበረሰባቸው የሚጠቅም ፕሮጀክት መቅረፅና ማስተዳደር እንዲችሉ በዲላ ከተማ የሚገኙ የአካል ጉዳተኞች ማሕበራት አባላትና አመራሮች በፕሮጀክት ዕቅድ አዘገጃጀት በቂ እውቀትና ክህሎት ባላቸው የዩኒቨርስቲው መምህራን የተሰጠ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሆኑን አስረድተዋል።
ስልጠናውን ከሰጡ መምህራን መካከል መምህር ታሪኩ ገ/መድህን፣ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ መምህርና ተመራማሪ፤ ስልጠናው በፕሮጀክት ዕቅድ አዘገጃጀት መሰረታዊ እውቀትና ክህሎት ለመያዝ የሚያስችል የፕሮጀክት ዓላማ፣ የእቅድ ዓላማ፣ የፕሮጀክት ምንነትን፣ የፕሮጀክት አዘገጃጀት፣ የፕሮጀክት ፋይናንስ አፈላለግና ሌሎች ተያያዥ ርእሰ ጉዳዮችን የዳሰሰ ስልጠና እንደነበር ገልጸዋል።
ከሰልጣኞች መካከል መምህርት ፀሀይ ታደሰ እና መምህር ግርማ አበራ በሰጡን አስተያየት፤ ስልጠናው ህይወታቸውን ለማሻሻል የሚጠቅም በተግባር የተደገፈ ጥሩ እውቀትና ክህሎት ያገኙበት ስልጠና መሆኑን ገልጸዋል።
በስልጠናው በዲላ ከተማ የሚገኙ አካል ጉዳተኛ ማሕበራት አባላትና አመራሮች፣ የማሕበራዊ ጉዳይ ተወካዮች፣ የሴቶች ጉዳይ ተወካዮችና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲዲላ፤
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
Facebook: https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://www.t.me
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et







