ዲ.ዩ፤ የካቲት 04/2016 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት አጋርነት ዳይሬክቶሬት ከጌዴኦ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች፣ ከምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ እና ከሲዳማ ክልል ዳራ ወረዳ ለተወጣጡ የማዘጋጃ ቤት እና የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች በተቀናጀ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ዙሪያ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የጌዴኦ ዞን ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ታደሰ፤ የጌዴኦ ዞን በርካታ እንግዶችና ቱሪስቶች የሚመላለሱበት አካባቢ እንደመሆኑ መጠን ከተሞችንና አካባቢን ጽዱ ለማድረግ ለሚሰሩ ስራዎች ስልጠና ለማግኘት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ስልጠናው መዘጋጀቱንና ይህም እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
አቶ ዮሐንስ አክለውም፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ የጌዴኦ ማህበረሰብ ተፈጥሯዊ መልክዓ ምድር በዓለም ቅርስነት ለመመዝገቡም ሆነ የአርሶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ እየሰራ ያለው ስራ ከፍተኛ በመሆኑ የሚያስመሰግነው ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት አጋርነት ዳይሬክቶሬት የአጫጭር ስልጠናዎች ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ብሩህ ተስፋሁን፤ ስልጠናው የዞኑ ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ጽ/ቤት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የተዘጋጀ ስልጠና መሆኑን ጠቁመው፤ ከተለያዩ ወረዳዎች ለተወጣቱ የማዘጋጃ ቤት እና የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች የተቀናጀ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድን መሰረት ያደረገ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የተሰጠ ስልጠና መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከአሰልጣኞች መካከል ዶ/ር ነጋሳ እሸቱ እና ዶ/ር ቴዎድሮስ በቀለ፤ ቆሻሻ ከተጠቀምንበት ሀብት መሆኑን ጠቁመው፤ ቆሻሻን ለሀይል ምንጭነትና ለማዳበሪያነት ግልጋሎቶች ማዋል እንደሚቻል ገልጸዋል። በተጨማሪም በአካባቢያችን ቆሻሻን መልሶ የመጠቀም ሂደት ወደ ዘመናዊነት የተቀየረ አይደለም ሲሉ አስረድተዋል።
በስልጠናው መዝጊያ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ተካልኝ ታደሰ፤ የየዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት አጋርነት ዳይሬክተር በበኩላቸው ከመሬት እየተጠቀምን ግን ለመሬት እየሰጠናት ያለነው ነገር ውስን ከመሆኑ የነሳ ምርትና ምርታማነት መቀነሱን ገልጸው፤ በአከባቢው የሚገኘውን ቆሻሻ በአግባቡ ወደ ኮምፖስት በመቀየር መሬቱ መልሶ እንዲለማ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።
አቶ ተካልኝ አክለውም፤ ሰልጣኞች ወደ ላካቸው ተቋም ሲመለሱ በስልጠናው ያገኙትን እውቀት ለሌሎች ባለሙያዎች በማጋራት ተግባራዊ ለማድረግ አቅደው ወደ ስራ መግባት እንደሚኖርባቸዋል አሳስበዋል።
ካነጋገርናቸው ሰልጣኞች መካከል ከከቡሌ ወረዳ ማዘጋጃ ቤት የመጡት አቶ ነጻነት ታደሰ እና ከገደብ ወረዳ አከባቢ ጥበቃ ጽ/ቤት የመጡት ወ/ሮ በረከት ዘውዴ፤ በስልጠና መደሰታቸውንና በቂ እውቀትና ግንዛቤ ያገኙበት ስልጠና እንደነበር ገልጸውልናል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ለወቅታዊ መረጃዎች
Facebook:
https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://t.me/dprd9
website: https://www.du.edu.et
Email: pirdir@du.edu.et







