ዲ.ዩ፤ ጥር 23/2016ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ ከከየካቲት 06-09/2016 ዓ.ም እንደሚሰጥ የተገለጸውን የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና (Exit Exam) ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን ዲላ ዩኒቨርሲቲ አሳውቋል።
ታምራት በየነ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት የመውጫ ፈተናን በተመለከተ ለዩኒቨርሲቲው የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ እንደ አገር በ2016 ዓ.ም አጋማሽ ዓመት የሚሰጠውን የመውጫ ፈተና በስኬት ለማጠናቀቅ በፕሬዚዳንት፣ በአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም በአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት የሚመሩት ዓበይት ግብረ ሀይሎች፣ ንዑስና የቴክኒክ ኮሚቴዎችን በማደራጀት ሰፊ ዝግጅቶች መከናወናቸውን ገልጸው፤ በዓመቱ አጋማሽ የሚመረቁ የሕክምና፣ የኪነ ህንፃ ምህንድስና እና በሌሎች ስድስት ፕሮግራሞች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ አራት መቶ የሚሆኑ የዩኒቨርስቲው ዕጩ ምሩቃን ተማሪዎች ለማስፈተን ሙሉ በሙሉ የዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
ከመደበኛ ተማሪዎች በተጨማሪ በቅዳሜና እሁድ መርሐ ግብር ትምህርታቸውን በተለያዩ ማዕከላት ሲከታተሉ የቆዩ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ስርዓትን እንዲለማመዱ በማሰብ የICT ላብራቶሪዎችን በማደራጀትና ሞዴል ፈተናዎችን በመስጠት ለፈተና የማዘጋጀት ስራ መከናወኑን ዶ/ር ታምራት አያይዘው ገልጸዋል።
እንደ ዶ/ር ታምራት ገለጻ፤ ከባለፈው ዓመት ልምድ በመውሰድ በመውጫ ፈተና የፈተና ንድፍ (Exam blueprint) ከእያንዳንዱ ትምህርት የሚጠበቅ ብቃት (Compitency) መሰረት ተማሪዎች አስፈላጊ ግብዓቶች እንዲደርሷቸውና በቂ ማካካሻ ትምህርት (Tutorial) እንዲሰጣቸው መደረጉንና ለመምህራን የሞዴል ፈተና አዘገጃጀት ስልጠና መሰጠቱን አንስተዋል።
ዶ/ር ታምራት አክለውም፤ በተለያዩ የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች የመውጫ ፈተና ወስደው የማለፍያ ነጥብ ያላመጡና በዘንድሮው አጋማሽ ዓመት ፈተናውን በዲላ ዩኒቨርሲቲ ለመውሰድ የሚፈልጉ ተፈታኞች ትምህርት ሚኒስቴር ባዘገጀላቸው ስርዓት ሲመዘገቡ በሚሰጠው አቅጣጫ መሰረት ዲላ ዩኒቨርሲቲ ፈተናውን ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አስገንዝበዋል።
መምህር በቀለ ወርቁ፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኑኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በበኩላቸው፤ ለሚሰጠው የመውጫ ፈተና በ19 የኮምፒውተር ላቦራቶሪዎች 435 ኮምፒውተሮች ተዘጋጅተው ባለፈው ዓመት በዩኒቨርሲቲው ባለሙያዎች በበለጸገው I-Exam ሶፍትዌር በመጠቀም በዩኒቨርሲቲው መምህራን የተዘጋጁ ሞዴል ፈተናዎች መሰጠታቸውን ገልጸዋል።
መ/ር በቀለ አያይዘውም፤ የመብራት መቆራረጥ፣ የኢንተርኔት መዘግየትና መቆራረጥ እንዳይከሰት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነና ለዚህም በቂ የ ICT ባለሙያዎች በመመደብ ከጥር 27-30/2016 ዓ.ም በትምህርት ሚኒስቴር የሚሰጠውን ሞዴል ፈተና እንዲሁም ከየካቲት 06-09/2016 ዓ.ም የሚሰጠውን ዋናውን የመውጫ ፈተና ለማስፈተን ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸውልናል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ




