ሀብታሙ ተመስገን (ዶ/ር )፤ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ኘሬዝዳንት ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት፤ ለ 2017 ዓ/ም የትምህርት ዘመን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በማስተላለፍ አሁን ላይ እንደ ሀገር ከትምህርት ሴክተሩ ጋር ተያይዞ በርካታ ትምህርት ቤቶች ላይ ብዙ ችግሮች እና እጥረቶች እንዳሉ ቢታወቅም በተለይ ለአካል ጉዳተኞች ፈተናው ብዙ በመሆኑ እንደ ዲላ ዩኒቨርሲቲ አቅም የፈቀደውን ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።
ዶ/ር ሀብታሙ አክለውም፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ለአቅመ ደካማና ለአካል ጉዳተኛ ቤተሰብ ተማሪዎች ይህን የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ያደረገው በቂ ነው በሚል ሳይሆን ምናልባት ሌሎች አካላትን ለማነቃቃት አቅም ካለው በሚል እሳቤ እንደሆነ ተናግረዋል።
አቶ ሙልጌታ ሽንጡ፤ የዲላ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ፣ የመንግስት ረዳት ተጠሪና የዲላ ከተማ ተወካይ እንደገለጹት፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ባሻገር እንደነዚህ አይነት ማህበራዊ አገልግሎት በመወጣት አሁን ላይ በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ አውስተው፤ ከእነዚህም ውስጥ ባሳለፍነው ዓመት በዲላ ከተማ አፄ ዳዊት ት/ቤት ላይ የሚገኙ ህንጻዎችን ከትምህርት ቤቱ በመረከብ እንደ አዲስ ገንብቶ ለትምህርት ቤቱ ማስረከቡ የሚታወቅ እንደሆነ ተናግረዋል።
አቶ ሙልጌታ አያይዘውም፤ ዩኒቨርሲቲው በዘንድሮው አመትም በዲላ ከተማ የመማር ፍላጎት እያላቸው ነገር ግን በትምህርት ቁሳቁስ እጦት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ለሚቀሩ ተማሪዎች የትኛውም ተማሪ ቤት መቅረት የለበትም በሚል እሳቤ ይህን ድጋፍ ለአቅመ ዳካማና ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ማድረጉ ለሌሎችም ጭምር ምሳሌ የሚሆን ተግባር እንደ ዲላ ከተማ አስተዳደር ዩኒቨርሲቲውን አመስግነዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክተር አቶ ተካልኝ ታደሰ በበኩላቸው፤ በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አገልግሎት ካሉ ስራዎች መካከል የበጎ ፍቃድ ስራዎች አንዱ እንደመሆኑ መጠን ዛሬ በዲላ ከተማ ለሚገኙ 200 ለሚደርሱ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ገልጸው፤ ከእነዚህም ውስጥ 103 የሚሆኑት አካል ጉዳተኛ ሲሆኑ የተቀሩት 97 የሚደርሱት ደግሞ የመግዛት አቅም የሌላቸው ተማሪዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የዚህ ድጋፍ ዋና አላማ በመደጋገፍ ለሌሎች መድረስ መቻልን በማስተማር ተማሪዎች በትምህርት ቁሳቁስ መግዛት አለመቻል ምክንያት ከትምህርት ገበታ እንዳይስተጓጎሉ ለማስቻል የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው ሲሉ አቶ ተካልኝ ገልጸዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው ተማሪዎች መካከል ተማሪ ሀይማኖት ጌዴቾ እና ተማሪ ይስሀቅ ሽፈራው፤ በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸው፤ ትምህርታቸውን ጠንክረው በመማር ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንደሚጥሩ ተናግረዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው ወላጆች መካከል አቶ ንጉሴ ባዩ እና ወ/ሮ እቴነሽ ገ/አምላክ፤ የኑሮ ውድነቱ ልጆቻቸውን በአግባቡ ለማስተማር ችግር ተፈጥሮባቸው እንደነበር በመግለፅ አሁን ግን በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
FB: https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram:https://t.me/dprd9
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et





