ዲ.ዩ፤ ነሐሴ 11/2016 ዓ/ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የቡና ምርምርና ስልጠና ተቋም ከ ጂ አይ ዜድ (GIZ) ጋር በመተባበር ላዘጋጀው የአራተኛ ዙር የግብርና ባለሙያዎች የክረምት ስልጠና ሰልጣኞች አቀባበልና ገለጻ አድርጓል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ቡና ምርምርና ስልጠና ተቋም ዋና ዳሬክተር አለሙ ደሳ (ዶ/ር)፤ ለሰልጣኞች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈው፤ አባቶቻችን ቡናን በማምረት የታወቁ ቢሆኑም ምርቱና ውጤቱ ከድካማቸው ጋር የሚጣጣም እንዳልነበር ጠቅሰው ይህ ደግሞ ዘርፉ በዕውቀት ባለመመራቱ እንደሆነ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቡና ምርት በዓለም 5ተኛ ከአፍሪካ 1ኛ ደረጃ ላይ የምትቀመጥ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር አለሙ፤ ከቡና ምርት ማግኘት የነበረባትን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በሚፈለገው መጠን አለማግኘቷን አያይዘው ተናግረዋል።
ዶ/ር አለሙ አክለውም፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ጭምር ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ረገድ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ስልጠናዎችን በመስጠት ጭምር የተሻለ መሆኑን አንስተዋል። አሁንም ከጂ አይ ዜድ ጋር በመተባበር የክረምት የስልጠና መርሐ ግብር ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ኘሬዝዳንት ልዩ ረዳት ዶ/ር አለማየሁ አካሉ በበኩላቸው፤ ቡና ለኢትዮጵያ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ፋይዳ ያለው እስትራቴጂክ ሰብል መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን አረንጓዴ ወርቅ የሆነ ሐብታችንን ለማስጠበቅ ውጤቱ የተሻለ እንዲሆን የዲላ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ ከማስተማር ጀምሮ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት በዘርፉ ከፍተኛ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ የቡና ምርምርና ስልጠና ተቋም የስልጠና ኦፊሰር የሆኑት መምህርና ተመራማሪ ኩምሳ ወ/ጊዮርጊስ፤ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማስቀጠል ዘርፉ ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው እንደመሆኑ መጠን ለዚህ ስልጠና ሰፊ ትኩረት በመስጠትና ሞጅሎችን በማዘጋጀት ስልጠናውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ቡና 40 በመቶ በማሳ ላይ እንዲሁም 60 በመቶ ከተለቀመ በኋላ በሚኖሩ የአያያዝ ጉድለቶች ጥራቱን ሊያጣ እንደሚችል የገለጹት ተመራማሪው፤ ስልጠናው ሰልጣኞች ከዚህ በፊት ከነበራቸው የተሻለ እውቀትና ግንዛቤ እንዲያገኙ እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
FB: https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram:https://t.me/dprd9
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et