ዲ.ዩ፤ ነሐሴ 15/2016 ዓ/ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በክረምት ልዩ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና በዲላ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው ስልጠናቸውን ሲከታተሉ ለቆዩ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንና አመራሮች የማጠቃለያ ፈተና ተሰጥቶ ስልጠናው ተጠናቋል።
ችሮታው አየለ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት፤ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና የተጀመረውን የትምህርት ሪፎርም ለማሳካት የመምህራንና የትምህርት አመራሮችን አቅም ለማጎልበት ታስቦ ሲሰጥ የቆየው ስልጠና በስኬት መጠናቀቁን በመግለፅ ለሰልጣኝ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች መልካም የስራ ዘመን እንዲሆንላቸው ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ታምራት በየነ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት በበኩላቸው፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በክረምት ልዩ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተውጣጡ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንና አመራሮችን ተቀብሎ የሚያስፈልገውን አገልግሎት በመስጠት፣ አስፈላጊ የስልጠና ግብዓት በማዘጋጀትና አሰልጣኝ ባለሙያዎችን በመመደብ በትምህርት ሚኒስቴር በተቀመጠው መርሐግብር መሰረት ስልጠናው በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ በዛሬው ዕለት በማዕከል የተዘጋጀውን የማጠቃለያ ፈተና መስጠቱን ገልፀዋል።
አቶ ገብሬ ነጋሽ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ፤ እንደ ሀገር በ28 ዩኒቨርሲቲዎች ለመምህራን 120 ሰዓት፣ ለትምህርት ቤት አመራሮች ደግሞ 60 ሰዓት በተማሩበት ሙያ (Subject matter)፣ በትምህርት ስነ ዘዴ (Pedagogy) እና በትምህርት ዲጂታላይዜሽን ርዕሰ ጉዳዮች ተምረው በዩኒቨርስቲው ተከታታይ ምዘና 30 ከመቶ ተይዞላቸው 70 ከመቶ በትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀውን ፈተና በበይነ መረብ (Online) መሰጠቱን ተናግረዋል።
አቶ ገብሬ አያይዘውም፤ ተከታታይ ምዘናውንና ማጠቃለያ ፈተናውን በድምሩ 70 ከመቶና ከዛ በላይ ላመጡ ሰልጣኞች የእውቅና ሰርተፊኬት እንደሚሰጣቸውና ይህም ቀጣይ ለሚሰጠው የደረጃ እድገት የራሱ ጥቅም እንደሚኖረው በማስገንዘብ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ስልጠናው በስኬት እንዲጠናቀቅ ላደረገው አስተዋጽኦ በትምህርት ሚኒስቴር ስም አመስግነዋል።
አቶ ጣሰው ባንጃ፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የተከታታይና ርቀት ትምህርት ኦፊሰር እና የልዩ ስልጠናው አስተባባሪ፤ 62 ርዕሳነ መምህራን እና 361 የተፈጥሮ ሳይንስ መምህራን ልዩ ስልጠናውን እንደወሰዱ አስታውሰው እነዚህ ሰልጣኞች ስልጠናውን ከመውሰዳቸው በፊት ቅድመ ፈተና (pre-test) እንደተፈተኑና ስልጠናውን ከተከታተሉ በኋላ በዛሬው እለት እየተሰጣቸው ያለው የስልጠናው ማጠናቀቂያ ድህረ ፈተና (Post-test) እንደሆነ ገልጸዋል።
ስልጠናውን ከሰጡት ባለሙያዎች መካከል አስናቀ ሙሉዬ (ዶ/ር)፣ በዋናነት በተማሩበት ሙያ፣ በትምህርት ስነዘዴና በትምህርት ዲጂታላይዜሽን ላይ ትኩረት በማድረግ ሞጅሎችን በማዘጋጀት ተግባር ተኮር ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
ከሰልጣኝ መምህራን መካካል መምህር ተሰፋዬ ከበደ እና መምህርት ሄለን ፀጋዬ በሰጡን አስተያየት፤ ስልጠናው በዘርፉ በቂ ልምድና እውቀት ባላቸው ባለሙያዎች በመሰጠቱና ተግባር ተኮር በመሆኑ በቂ ተሞክሮ ያገኙበት እንደሆነ ገልጸውልናል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
FB: https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram:https://t.me/dprd9
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et