ዲ.ዩ፤ ሚያዝያ 22/2016 ዓ/ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ በማሕበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብዕ ኮሌጅ እና በተፈጥሮ ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ስር በሚገኙ ትምህርት ክፍሎች በመምህርነት ሙያ የሚሰለጥኑ ተማሪዎች የነበረውን የተግባር ትምህርት (Practicum) ማጠናቀቃቸው ተገልጿል።
ታምራት በየነ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት፤ በታሪክ አጋጣሚ ዲላ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ትምህርትና ጤና ኮሌጅ በመሆን በመቋቋም በዘርፉ እንደ ሀገር ሰፊና ጉልህ አስተዋፅኦ ሲያበረክት መቆየቱን ጠቅሰው፤ ይህን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ለማስቀጠልና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተከናወነ ባለው ሪፎርም መሰረት ዲላ ዩኒቨርሲቲ በተሰጠው የተልዕኮ መስክ ልየታ አንዱ በሆነው የመምህራን ትምህርት የትኩረት አቅጣጫ በማስቀመጥ ተልዕኮውን ማሳካት የሚችል ወጥ አደረጃጀት እያቋቋመ እንዲሁም የአስር ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ በመከለስ ወደ ስራ ለማስገባት እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
ዶ/ር ታምራት አክለው፤ የአፕላይድ ዩኒቨርሲቲ ስርዓተ ትምህርት 40 በመቶ በንድፈ ሀሳብ እንዲሁም 60 ከመቶ የተግባር ትምህርት እንዲሆን የተቀመጠ ስለሆነ ይህን ያማከለ የመስክ፣ የቤተ ሙከራ ልምምድ፣ ኢንተርንሺፕ፣ ኤክስተርሺፕ እና ፕራክቲከም አጠናክሮ በመስጠት የትምህርት ጥራትን ለማስጠቅ የተቀናጀ ስራ እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።
በዚህም መሰረት እጩ መምህራን በአካባቢው በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመሄድ የተሳካ የተግባር ትምህርት መከወናቸውን ገልጸው፤ ይህን የተሳካ የተግባር ትምህርት እውን እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉት የመስክና የቤተሙከራ ዳይሬክቶሬት፣ የማሕበራዊ ሳይንስና ሥነ-ስብዕ ኮሌጅ፣ የተፈጥሮ ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ፣ ትምህርት ክፍሎች፣ መምህራን፣ ትምህርት ቤቶች፣ የዞን ትምህርት መምሪያዎች፣ የወረዳና የከተማ ትምህርት ጽ/ቤቶች፣ እጩ መምህራንና ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
መምህር አሸናፊ አስራት፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የመስክና ቤተ ሙከራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎች እንዲሆኑ ለማስቻል የተግባር ትምህርት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በዩኒቨርሲቲዎች የተልዕኮ ልየታ መሰረት የተግባር ዩኒቨርሲቲ (Applied Science) በመሆን አተኩሮ ከሚሰራባቸው ዘርፎች መካከል የመምህራን ትምህርት ዘርፍ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
መምህር አሸናፊ አያይዘውም፤ በማሕበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብዕ ኮሌጅ እና በተፈጥሮ ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ስር በሚገኙ ትምህርት ክፍሎች 188 የ4ኛ ዓመት ተማሪዎች ሶስተኛውና የመጨረሻ የተግባር ትምህርት እንዲሁም 86 የሶስተኛ ዓመት ተማሪዎች 2ኛ የተግባር ትምህርት ከመጋቢት 23/2016 ዓ/ም እስከ ሚያዝያ 22/2016 ዓ/ም ለአንድ ወር የተሳካ የተግባር ትምህርት መውሰዳቸውን አስገንዝበዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊ ግብአቶችን በማሟላት አስፈላጊ ድጋፍና ክትትል በማድረግ የተግባር ትምህርቱ አበረታች ውጤት በማስመዝገብ እንደተጠናቀቀ መምህር አሸናፊ አክለው ገልጸዋል።
ኢዮብ ቀለመወርቅ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማሕበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብዕ ኮሌጅ ዲን በበኩላቸው፤ ኮሌጁ ካሉት አስር ትምህርት ክፍሎች በስድስት ትምህርት ክፍሎች በቅድመ ምረቃ ፕሮግራ የመምህራን ትምህርት ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ዓመት በመምህርነት ሙያ ለሚሰለጥኑ ተማሪዎች በሶስት ደረጃ ከፍሎ የተግባር ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል።
በማሕበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብዕ ኮሌጅ በመምህርነት ሙያ በሚሰጡ፤ በጂኦግራፊ፣ በታሪክና ቅርስ አስተዳደር፣ በሥነ-ዜጋ፣ በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛና በአፋን ኦሮሞ በሁለተኛ የተግባር ትምህርት (practicum II) 49 ተማሪዎች፣ እንዲሁም በሶስተኛው ደረጃ የተግባር ትምህርት 107 ተማሪዎች በይርጋጨፌ፣ በወናጎ፣ በጓንጓ፣ በዲላና በቆፌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተመድበው የተግባር ትምህርት ልምምድ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ዶ/ር ኢዮብ ተናግረዋል።
ዶ/ር ኢዮብ አክለውም፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በመምህራን ስልጠና ስመጥር እንደሆነና ከዚህ ተቋም የሚመረቁ ተማሪዎች ከፍተኛ ተፈላጊነት የነበራቸው መሆኑን አውስተው፣ ተመራቂዎቻችን በዚያን ያህል ተፈላጊነት የነበራቸው ከክፍል ውስጥ የንድፍ ሀሳብ ትምህርት በተጨማሪ ደረጃውን የጠበቀ የተግባር ልምምድ ያደርጉ ስለነበረ እንደሆነ አስረድተው ለዚህም የየትምህርት ክፍሎቹ ጠንካራ መምህራን የማይተካ ሚና ስለነበራቸውና ትምህርት ክፍሎቹም የተግባር ስልጠናውን በአግባቡ ስላስኬዱት እንደነበር አብራርተዋል።
ወንድወሰን ገበያው (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን፤ በየተፈጥሮ ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ስር አምስት የትምህርት ክፍሎች፤ ባዮሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ሒሳብና ስፖርት ሳይንስ 37 ተማሪዎች በሁለተኛው የተግባር ትምህርት፣ 81 ተማሪዎች ሶስተኛውን የተግባር ትምህርት መውሰዳቸውን አንስተው፤ የተግባር ትምህርት ሰልጣኝ እጩ መምህራን ከቀለም እውቀት ተጨማሪ በሰው ፊት መቆም፣ ሀሳብ በተደራጀ መልኩ የመግለጽ ክህሎት፣ የተማሪዎችን ባህሪ መረዳት፣ የመማሪያ ክፍል አስተዳደር ክህሎት፣ የግል ህይወታቸውን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ መምራት እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች የተማሩበት እንደሆነ ገልጸዋል።
ኤርሚያስ ታደሰ፣ የይርጋጨፌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ቤቱ የመደባቸውን እጩ መምህራን መደበኛ መምህራን ተክተው ክፍል ገብተው ሲያስተምሩ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጡ፣ በተለያዩ የተማሪዎች ክበባት ሲሳተፉ መቆየታቸውን ተናግረው፣ በተደረገው ክትትልና ግምገማ እጩ ምሩቃኑ ለሙያቸው ከፍተኛ ክብር ያላቸው እጩ መምህራን እንደሆኑ ገልጸው በቂ እውቀትና የማስተማር አቅም ያላቸውን ለነገ አገር ተረካቢ ትውልድ የሚቀርፁ ምሁራን ለማፍራት ዲላ ዩኒቨርሲቲ ለሚያደርገው ጥረት ትምህርት ቤታቸው በአጋርነት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በይርጋጨፌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተግባራዊ ልምምድ ስታደርግ ያገኘናት ዕጩ መምህርት ሳሌም ፀሐዬ፣ ከባዮሎጂ ትምህርት ክፍል፤ ተግባራዊ ልምምዱ በክፍል ውስጥ ስትማረው የነበርን ንድፍ ሀሳብ ወደ ተግባር እንዴት እንደሚቀየርና የመምህርነት ሙያ ምን እንደሚመስል ያየችበት ቆይታ እንደነበር ገልጻልናለች።
በተመሳሳይ በወናጎ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ያገኘነው እጩ መምህር ቢንያም ፈንታ፣ ከጂኦግራፊ ትምህርት ክፍል የተግባር ልምምዱ በንድፈ ሀሳብ የተማረውን ወደ ተግባር እንዴት እንደሚቀይር፣ በውስጡ ያለውን እውቀት እንዴት ወደ ተማሪዎች ማስተላለፍ እንዳለበት፣ የክፍል አስተዳደርና የተማሪዎች ባህሪ ማወቅ፣ የትምህርት እቅድ ማውጣት፣ የስራ ስዓት አጠቃቀም፣ የህይወት ተግዳሮቶች መቋቋም፣ የአካባቢው ባህልና ትውፊት መረዳት የመሳሰሉት በርካታ ልምዶች እንደቀሰመ ነግሮናል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ፤
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
Facebook:
https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://www.t.me
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et