ዲ.ዩ፤ የካቲት 12/2016 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት እና በምርምር፣ ህትመት፣ ሥነ ምግባርና ሥርፀት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት በዩኒቨርሲቲው በተመደበላቸው በጀት የሚሰሩ ምርምሮች 13ኛው ዓመታዊ የምርምር ቫሊዴሽን እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ችሮታው አየለ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት፣ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ የዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ስራ እንዲሳለጥ የተቻለው ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አንስተው፤ በመንግስት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ከነችግሩ ቢሆን ለምርምር ስራዎች ከፍተኛ በጀት በመመደብ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
ዶ/ር ችሮታው አክለውም፤ ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ ለምርምር ከሚበጅተው በጀት ባሻገር ተመራማሪዎች እና መምህራን ሌሎች የምርምር በጀት አማራጮችን ማየት እና ጠንክሮ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመው፤ እንደ አፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ አሰራር በአብዛኛው የምርምር ፈንዶች መገኘት ያለባቸው ከኢንዱስትሪው እና ከግሉ ሴክተር እንደሆነ አስረድተዋል።
ዶ/ር ችሮታው በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይም ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ወደ ዩኒቨርሲቲው ለማምጣት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ በመምህራን እና በተመራማሪዎች የሚሰሩ ምርምሮች ወደ መሬት ወርደው ለውጥ እንዲያመጡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ በማስገንዘብ የመማር ማስተማር ስራን ከመወጣት ጎን ለጎን መምህራን ምርምሮችን ተግተው እንዲሰሩ አደራ ብለዋል፡፡
ሀብታሙ ተመስገን (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት የዕለቱ ቁልፍ መልዕክት (keynote) አቅራቢ፤ በበኩላቸው የምርምር ቫሊዴሽን በተቋም ደረጃ በውድድር ሂደት በመድረክ ተተችተው፤ ከተቋሙ ዋና የትኩረት አቅጣጫ አንፃር ተፈትሸው፤ በጀት የተመደበላቸው ምርምሮች በተገቢው ሂደት መሄዳቸው፣ ውጤት ያላቸው መሆኑ፣ በቂና ትክክለኛ መረጃ የተሰበሰበባቸው እና የመሳሰሉ ተያያዥ ጉዳዩች ግምገማ የሚደረግበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
ምስጋኑ ለገሰ (ዶ/ር)፣ የምርምር ህትመት፣ ስነ-ምግባርና ሥርፀት ዳይሬክተር በበኩላቸው፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ አስፈላጊውን በጀት በመመደብ ተመራማሪዎች ማህበረሰብ ተኮር የሆኑ የተለያዩ ምርምሮች እንዲያካሂዱ ከማድረግ ባለፈ እነዚህ ተመራማሪዎች የሚሰሯቸውን ምርምሮች ቫሊዴት ማድረጉ የምርምሮቹን ተዓማኒነት የሚያጎለብት መሆኑን ገልጸዋል።
በምርም ቫሊዴሽኑ የመክፈቻ መርሃ ግብር ላይም ዋቅሹማ ያደሳ (ዶ/ር) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ኬሚስትሪ መምህርና ተመራማሪ፣ ከሌሎች ተመራማሪዎች ጋር በአፈር እና ውሃ አጠባበቅ ዙሪያ የሰሩትን ምርምር፣ አቶ ሀይለማርያም ሙሉጌታ፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ አጠቃላይ ሆስፒታል የአንስቴዢያ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ፤ በደቡብ ክልል ያሉ ሶስት የህክምና ትምህርት የሚሰጥባቸውን የጤና ተቋማት ማዕከል በማድረግ በጤናው ዘርፍ ያሉ ክፍተቶችን በተመለከተ ከሌሎች መምህራንና ተመራማሪዎች ጋር የሰሩትን ምርምር እንዲሁም አለሙ ደሳ (ዶ/ር)፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የቡና ምርምርና ስልጠና ተቋም ዳይሬክተር ደግሞ የቡና ምርታማነትን እና ጥራትን ጠብቆ ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ከሌሎች ምሁራን ጋር የሰሩትን ጥናት አቅርበዋል።
በእለቱ ቁልፍ መልዕክት አቅራቢ እና ሶስቱ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን ያቀረቡ ምሁራን ባነሷቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከመምህራን እና ጥሪ ከተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ጥያቄዎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በመድረኩ ከተገኙ ባለድርሻ አካላት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ በድሉ ገዛኸኝ፣ ከምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት መምጣታቸውን ገልጸው፤ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃም ሆነ በጤና ዙሪያ የሚሰሩ ጥናቶች ተሰርተው የሚቀመጡ ሳይሆን ወደ ተግባር የሚለወጡ ከሆነ የማህበረሰብን ችግር መቅረፍ እንደሚችሉ ሐሳባቸውን አጋርተውናል።
በምርምር ቫሊዴሽን መርሃ ግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ ዲኖች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ የምርምር ዘርፍ ኃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም መምህራንና ተመራማሪዎች እየተሳተፉ ነው።
በቀጣይም የምርምር ቫሊዴሽኑ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ በየኮሌጁ በሰባት የተለያዩ የመወያያ ስፍራዎች ተከፋፍሎ እስከ ነገ ድረስ እንደሚቀጥ ከአስተባባሪዎች ተገልጿል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
FB: https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram:https://t.me/dprd9
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et