ዲ.ዩ፤ ጥር 25/2016 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ በአቅም ማሻሻያ (Remedial) መርሃ ግብር ዲላ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው ለመጡ ተማሪዎች ገለጻ (Orientation) ተሰጥቷል።
አቶ አማኑኤል ጌካ፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተር፤ የ 2016 ዓ.ም የሪሜዲያል መግቢያ መስፈርቱን አሟልታችሁ ወደ ዩኒቨርሲቲያችን የመጣችሁ ተማሪዎች እንኳን ወደ አረንጓዴው ምድር ዲላ ዩኒቨርሲቲ በደህና መጣችሁ በማለት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል
አቶ አማኑኤል አያይዘውም፤ የተማሪዎች አገልግሎት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ተማሪዎችን ከመቀበል ጀምሮ መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ የተሳካ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው በቀጣይ ተማሪዎች በግቢ ቆይታቸው በማስታወቂያ ቦርድ ላይ የሚለጠፉ መልዕክቶችን በንቃት በመከታተል እንዲተገብሩ አደራ ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የ’ፍሬሽማን’ ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ዲን መ/ር መንግስቱ ተሾመ፤ በአቅም ማሻሻያ መርሃ ግብር የተመደቡ ተማሪዎች ከ27/05/16 ዓ.ም ጀምሮ ትምህርት እንደሚጀምሩ ገለጸው፤ ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው በሚሰጧቸው የተለያዩ ተከታታይ ምዘናዎች 30 ከመቶ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚሰጠው ፈተና ደግሞ 70 ከመቶ እንደሚያዝላቸው አብራርተዋል።
ከምዘናው በኋላም በድምር ውጤታቸው 50 ከመቶና ከዚያ በላይ ማምጣት የቻሉ ተማሪዎች የዩኒቨርስቲው የመጀመሪያ ዓመት (Freshman) ተማሪ ሆነው እንደሚቀጥሉ መ/ር መንግስቱ አክለው ገልፀዋል።
መ/ር መንግስቱ አክለውም የፍሬሽማን ጽ/ቤት በአቅም ማሻሻያ መርሃ ግብር አስተባባሪዎችን በመመደብ የመማር ማስተማር ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን ክትትል እና ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
አስናቀ ይማም (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ዋና ሬጅስትራር በበኩላቸው፤ በዩኒቨርሲቲው ለ 2016 ዓ.ም በአቅም ማሻሻያ መርሃ ግብር 1699 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች እና 1385 የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች፤ በድምሩ 3084 ተማሪዎች መመደባቸውን ገልፀዋል።
አቶ አዲስ ታምሩ፣ የሕግ ትምህርት ክፍል መምህርና የዩኒቨርሲቲው የህግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የዩኒቨርሲቲውን የተማሪዎች የዲሲፒሊን መመሪያ መሰረት በማድረግ ተማሪዎቹ በግቢ ውስጥ ሊከተሏቸው ስለሚገቡ የስነ ምግባር መርሆዎች ገለጻ አድርገዋል።
የማጠቃልያ ንግግር ያደረጉት ወ/ሮ ነዲ ገቢሳ፣ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ፤ ተማሪዎች በቆይታቸው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ጠንክረው በመስራት የልጅነት ህልማቸውን እውን ለማድረግ እንዲተጉ አደራ ብለዋል።
ገለጻውን ሲከታተሉ ካገኘናቸው ተማሪዎች መካከል ተማሪ ሄርሜላ አክሊል እና ተማሪ አስማማው ደምሴ፤ ከመጡበት ቀን ጀምሮ በተቋሙ የተደረገላቸው አቀባበል እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤ የተደረገላቸው ገለጻ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ሊኖራቸው የሚገባውን ስነምግባር እንዲገነዘቡ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።
በገለጻው ወቅት የዩኒቨርስቲው አመራሮች፣ ሰራተኞች፣ የተማሪዎች ሕብረት ተወካዮች፣ መምህራን፣ የፀጥታ አካላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።