ዲ.ዩ ሰኔ 1/2016 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የዕፅዋት ጥበቃና ኢኮቱሪዝም ማዕከል አዘጋጅነት “መሬትን መልሶ ማልማት፣ በረሃማነትንና ድርቅን መቋቋም” በሚል መሪ ሃሳብ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ51ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደግሞ ለ31ኛ ጊዜ የአካባቢ ቀን በተለያዩ ኩነቶች ተከብሮ ውሏል።
ሀብታሙ ተመስገን (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት፤ የአካባቢ ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚከበሩ ቀናት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ቀኑን በማክበር የተራቆተ አካባቢን ማህበረሰብን በማሳተፍ መለወጥ እንደሚቻል፣ የተራቆቱ መሬቶችን መልሰው እንዲያገግሙ በማድረግ አደጋ እንዳይደርስ ብሎም በአለም ደረጃ እየጨመረ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ እንዲቀንስ በማድረግ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚቻል ገልፀዋል።
ታሊሞስ ሴታ (ዶ/ር፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የዕፅዋት ጥበቃና ኢኮቱሪዝም ማዕከል ዳይሬክተር በበኩላቸው፤ አካባቢያችንን እንጠብቅ በሚል በየአመቱ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚደረግ ፕሮግራም መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን መሠረት በማድረግ በዩኒቨርሲቲያችን ላይ ከሚሰሩ የምርምር ማዕከላት አንዱ በሆነው የዕፅዋትና ኢኮቱሪዝም ማዕከል ይህን ቀን ለማስታወስ የተዘጋጀ ፕሮግራም ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ጌታሁን ሀይሌ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ተፈጥሮ ሀብት መምህርና ተመራማሪ፤ የአለም አቀፍ የአካባቢ ቀን የተራቆተ መሬት መልሶ እንዲያገግም በማድረግ በርሃማነት እና ድርቅን የሚቋቋም አካባቢና ማህበረሰብ መፍጠር (Land restoration, desertification and drought resilience) በተመለከተ የውይይት መነሻ ሃሳብ ጽሁፍ አቅበው በመድረኩ ተሳታፊዎች ላይ ውይይትና የሀሳብ ልውውጥ ተደርጓል።
ከፕሮግራሙ ተሳታፊዎች መካከል የዲላ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ትምህርት ክፍል 4ኛ ዓመት ተማሪ ይታያል መኳንት በሰጠን አስተያየት፤ ህብረተሰቡ ያለውን የተፈጥሮ ሀብቱን ለመጠቀም፣ የጠፋውን ለመተካትና ለወደፊት ደግሞ ምን ያህል ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ችግኞችን ከተከልን በኋላ ምን ያህል እንክብካቤ እየሰጠናቸው እንደሆነ ግንዛቤ ያገኘሁበት ነው ብሏል፡፡
በፕሮግራሙ በጌዴኦ ዞን የሚገኙ የመንግስት እና የግል ት/ቤቶች፣ መምህራን ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ትምህርት ክፍል ስለ አከባቢ ጥበቃ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ ተሰርቷል። ከዚህም በተጨማሪ የአካባቢ ክበብ አባላት የኪነጥበብና የስነጽሁፍ ስራዎችን ያቀረቡ ሲሆን አረንጓዴ ክለብም ተመስርቷል። በፕሮግራሙ መዝጊያም ተሳታፊዎች ሀገር በቀል ችግኞችን በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ፤
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
Facebook:
https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://www.t.me
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et
















