ዲ.ዩ፤ መጋቢት 20/2016 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ አጠቃላይ ሆስፒታል አዘጋጅነት በምርምር መረጃ አያያዝ እና አስተዳደር እንዲሁም በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዙሪያ ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቋል፡፡
አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅና አጠቃላይ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ፣ በስልጠናው ማጠናቀቂያ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ያደጉት አገራት በሰው ሰራሽ አስተውሎት (Al) ጭምር በመጠቀም መረጃዎችን እንዴት መያዝ እንደሚቻልና በጥሩ ተነሳሽነት ምርምሮችን እንዴት መስራት እንደሚቻል በኮሌጁ ለሚገኙ ተመራማሪዎች ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።
አቶ ትዝአለኝ አክለውም፤ አሰልጣኞች ዲላ ዩኒቨርሲቲን እንደተቋም በምን መንገድ ሊያግዙ እንደሚችሉ እና ሌሎች በርካታ ስራዎችን እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል።
ዶ/ር አትንኩት አላምረው፤ በጀርመን ግራፍስ ዋልድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪና የ’Post Doctoral’ ተመራማሪ በጥናትና ምርምር መረጃ አያያዝና አስተዳደር ዙሪያ እንዲሁም አቶ ኪሩቤል ብሩክ፣ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ የሰው ሰራሽ አስተውሎት በጤናው ዘርፍ በሚሉ ሐሳቦች ዙሪያ ልምዶቻቸውን አካፍለዋል።
ስልጠናውን የወሰዱት በነርሲንግ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ሲስተር ታክላ ታምር በሰጡን አስተያየት፤ እንደ ዩኒቨርሲቲ የምንሰራቸው ስራዎች ከምርምር ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ስልጠናው ትልቅ ግብዓት እንደሚሆናቸው ገልጸዋል።
በህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ት/ቤት መምህር የሆኑት አቶ ጌቱ ካሳ በበኩላቸው፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት በጤናው ስርዓት ውስጥ እንዴት መተግበር እንደሚቻል ልምድ የተካፈልንበትና ትልቅ ግብአት ያገኘንበት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከ 20 በላይ የሚሆኑ መምህራን ተመራማሪዎች እንዲሁም የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ለተከታታይ ሁለት ሳምንታት የተሰጠውን ስልጠና መከታተላቸው ታውቋል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ፤
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
Facebook:
https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://www.t.me
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et