ዲ.ዩ፤ መጋቢት 3/2016 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅና አጠቃላይ ሆስፒታል ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን “ሴቶችን እናብቃ፣ ልማትና ሰላምን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ሃሳብ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች አክብሮ ውሏል። ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ113ኛ ጊዜ እንዲሁም በሀገራችን ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ ተከብሯል።
በዓሉን በንግግር የከፈቱት የዲላ ዩኒቨርሲቲ የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅና አጠቃላይ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ113ኛ በአገራችን ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘው ይህ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በተመለከተ ቢያንስ አንድ ጊዜ ቆም ብለን ስለሴቶች መነጋገር የሚቻልበት መልካም አጋጣሚ ስለሆነ በዓሉን እንደ ተቋም ማክበር እንዳስፈለገ ገልጸው ለዚህም የሴቶች ፎረም ሚና ትልቅ እንደነበር አስረድተዋል።
አቶ ትዝአለኝ አክለውም፤ ተቋሙ የለውጥ ጎዳና ላይ እንደመሆኑ በሆስፒታሉ በተለያየ ሴክተር ላይ ሴቶችን ሳናካትት ለውጥ እንደማይኖር በማረጋገጥ ሴት እህቶቻችንን በሚሰሩበት ስራ በራሳቸው የተመሰገኑ እንዲሆኑና በአመራሩም ወደፊት እንዲመጡ ለማስቻል አሁን ላይ በተቋሙ አዲስ የሴቶች ፎረም ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።
ይህ ፎረም አቅሙን ሲያጠናክር በአመራር ደረጃ በተቋሙ ወደ 16% ያለውን የሴቶች ተሳትፎ በሂደት ወደ 30% ከፍ ለማድረግና በቆይታ ደግሞ ወደ 50% ለማሳደግ የሚኖረው ሚና ትልቅ እንደሆነ አያይዘው ተናግረዋል።
ወ/ሮ ዘመናይ ህርባዬ፣ የጌዴኦ ዞን ሴቶችና ህፃናት ም/ኃላፊ በበኩላቸው ፤ አሁን ላይ በየትኛውም ቦታ ያለሴቶች ተሳትፎ የሚመጣ ልማትም ይሁን ለውጥ ግቡን የሚመታ ባለመሆኑ እንደ ሀገር በአመት አንዴ በዓሉን ከማክበር ባለፈ በየቦታው ሴቶችን የማብቃትና የበቁትንም ወደፊት የማምጣት ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ወ/ሮ አለሚቱ ብርሃኑ፣ የዩኒቨርሲቲው የሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክተር በበኩላቸው፤ ይህ በዓል በአለም አቀፍ ደረጃ ጭምር በአንድነት የሚከበረው በአለም ያሉ መንግስታት የሴቶች ጉዳይ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እና የዴሞክራሲ ጉዳይ እንደሆነ አምነው በመቀበል በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ መድልዎችን እንዲያስወግዱና የሴቶችን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት እንዲያረጋግጡ ለማነሳሳት ነው ብለዋል።
“በሁለም ዘርፍ የበቁ ሴቶች አለምን ያበቃሉ” በሚል ርዕስ በመምህርት ኤደን አሸናፊ የመወያየ ጽሁፍ ቀርቦ በመድረኩ ተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል።
በተጨማሪም በሆስፒታሉ የመጀመርያዋ ብቸኛ የቀዶ ጥገና እስፔሻሊስት ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ኮከብ አያሌው፤ በበዓሉ ላይ ለተገኙ ተሳታፊዎች የሕይወት ልምዳቸውንና ተሞክሯቸውን አካፍለዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከልም ልዩ ልዩ ጣዕመ ዜማዎችን በማቅረብ የዝግጅቱ ድምቀት ሆኗል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲዲላ፤
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
Facebook:
https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://www.t.me
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et