ዲ.ዩ፡- ሐምሌ 2/2016ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ):- በዲላ ዩኒቨርሲቲ ከሐምሌ 3 እስከ 12/2016 ዓ.ም በበይነ መረብ እና በወረቀት ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና፣ በዩኒቨርሲቲው በአስፈጻሚነት ለተመደቡ የፈተና ማዕከል ኃላፊ፣ የፈተና ጉድኝነት ማዕከል አስተባባሪ፣ የፈተና ጣቢያ ኃላፊና ሱፐርቫይዘሮች ስለ ፈተና አስፈጻሚዎች መብትና ግዴታ እንዲሁም ስለተፈቀዱ እና ስለተከለከሉ ነገሮች በተመለከተ ገለጻ (Orientation) ተሰጥቷል።
በገለጻው ላይ ለተገኙ ፈተና አስፈጻሚዎች እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት መልዕክት ያስተላለፉት ችሮታው አየለ (ዶ/ር )፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት፤ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከመላ ሀገሪቱ ዲላ ዩኒቨርሲት ተመድባችሁ ለፈተና አስፈጻሚነት ስለመጣችሁ በዩኒቨርሲቲውና በራሴ ስም የተሰማኝን ደስታ መግለጽ እወዳለው በማለት ወደ አረንጓዴዋ ምድር ዲላ ዩኒቨርሲቲ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ እንደ ሀገር የትምህርት ስርዓቱን ይልቁንም ከትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ ያሉትን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት አንዱ መስራት አለበት ተብሎ የተያዘው የፈተና ስርዓቱን ጠንካራና ግልጽ እንዲውም ደግሞ ከስርቆየት የፀዳ ለማድረግ የሚስራው ስራ አንዱ እና ዋንኛው እንደሆነ በመግለጽ ለዚህም ወደ ዩኒቨርሲቲው ለፈተና አስፈጻሚነት ለመጡ በሙሉ መልካም የመፈተን ሳምንት እንዲሆንላቸው መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በመድረኩ ከትምህርት ሚኒስቴር በዲላ ዩኒቨርሲቲ ፈተና ማዕከል ኃላፊ ሁነው በተመደቡት በአቶ ሙሉዓለም መኮንን ፤ በዩኒቨርሲቲው የተመደቡ ፈተና አስፈጻሚዎች በፈተናው ወቅት ስላላቸው መብትና ግዴታዎች እንዲሁም አጠቃላይ በፈተና ወቅት ስለተከለከሉና ስለተፈቀዱ ነገሮችን በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ከፈተናው ጋር ተያይዞም በፈተና ጣቢያዎች ማንኛውም የፈተና ማዕከል ኃላፊ፣ የጉድኝት ማዕከል አስተባባሪ፣ ጣቢያ ኃላፊ፣ ሱፐርቫይዘሮች፣ ፈታኝ፤ የፊተና ግብአቶች ቆጣሪ እና ሌሎች የፈተና ግበረ ኃይል አባላት ወደ መፈተኛ ክፍል እና አካባቢ ስልክ፣ ፍላሽ፣ ታብሌት፣ እና ሌሎች ማንኛውንም ፎቶ፣ ምስል እና ድምጽ የሚቀርጹ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን መያዝና መግባት በጥብቅ የተከለከለ መሆኑ በመድረኩ ተብራርቷል።
በፈተና አስፈጻሚነት የተመደበ ማንኛውም ፈታኝ፤ ሱፐርቫይዘርና የፈተና ግብአቶች አደራጅ ማንኛውንም ዓይነት መጽሐፍት፣ መጽሔት እና ጋዜጣ በመፈተኛ ክፍል ይዞ መገኘት ሆነ መጠቀም የተከለከለ መሆኑም ተመላክቷል።
ለፈተና ደህንነት መረጋጥጥ አጋዥ በሆኑ አካሄዶች እንዲሁም የደንብ ጥሰት መከላከልን በተመለከት ሠፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፤ ፈተና አስፈጻሚዎች የፈተና ደንብ ጥሰትን የመከላከል ተግባር ላይ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ጥብቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ፤
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
Facebook:
https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://www.t.me
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et






