ዲላ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የተገበራቸውን ፕሮጀክቶች መርቆ አስረከበ

ዲ.ዩ፦ ሐምሌ 15/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት በኩል የተገበራቸውን ፕሮጀክቶች የምረቅና ርክክብ መርሃግብር አካሄደ።
አቶ ተካልኝ ታደሰ፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክተር፤ በዛሬው ዕለት በተካሄደው የርክክብ ምረቃ ሥነ-ስርዓት እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR ) እና ከአካባቢዎቹ አስተዳደር ጋር በመተባበር የገነባቸውን ነፃ የሕግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸውን ገልፀዋል።
ግንባታቸው ተጠናቆ ዛሬ የተመረቁት በዲላ እና ወናጎ ማዕከላት የተገነቡት ሲሆኑ በሌሎች ማዕከላትም የተጀመሩትን ግንባታዎች አጠናቆ ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ተካልኝ ማብራሪያ፤ ነፃ የሕግ አገልግሎቱ በዋነኝነት የገንዘብ አቅም ለሌላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ሴቶች፣ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ ተፈናቃዮችና ከስደት ተመላሾች፣ ለአረጋውያን እንዲሁም ኤች.አይ.ቪ ኤዲስ በደማቸው ላለባቸው ዜጎች እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል፤ ለአራት ዓመታት ሲለማ የቆየው ስነ-ህይወታዊ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ቨርሚ ኮምፖስት) ፕሮጀክት በወናጎ እና አባያ ወረዳዎች የርክክብ ስነ ስርዓት ተካሂዷል። ፕሮጀክቱ በአከባቢና ህብረተሰብ ጤና ላይ ትልቅ ችግር የሚፈጥር የቡና ገለፈትን ቨርሚ የተባሉ የመሬት ትሎችን ተጠቅሞ በስነ-ህይወታዊ ዘዴ ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያነት የሚቀይር ነው ተብሏል።
የቨርሚ ማዳበሪያው ከሐምሌ 2011 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሐምሌ 2015 ዓ.ም ድረስ የተተገበረ ሲሆን በጥቅሉ ከአንድ ሚሊዮን 459 ሽህ ብር በላይ ገንዘብ ወጪ ተደርጎበታል ተብሏል።
ከፕሮጀክቱ ርክክብ በኋላ የየአካባቢው አስተዳደርና ስልጠና የወሰዱ አርሶአደሮች እንዲያሰፉት የታለመ ሲሆን አስፈላጊ በሆኑ እና የዩኒቨርሲቲውን እገዛ በሚፈልጉ ጉዳዮች ዩኒቨርሲቲው እገዛ ያደርጋልም ተብሏል።
የተፈጥሮ ማዳበሪያው የአፈር ለምነትና ምርታማነትን የመጨመር፤ የአከባቢ ብክለትን የመቀነስ፣ ከዛም አልፎ ለወጣቶች ዘላቂ የስራ እድል የመፍጠር አቅም ያለው እንደሆነ ተብራርቷል።
በተጨማሪም፤ በዲላ ዩኒቨርሲቲ በ2015 በጀት ዓመት አቅመ ደካማና በኢኮኖሚ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ከሆኑት መካከል የአስር አባወራዎችና እማወራዎችን ቤቶች የማደስና መገንባት ስራ ተሰርቷል።
ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ልየታ በማድረግ በወናጎ ከተማ አምስት እና ይርጋጨፌ ከተማ አምስት፣ በድምሩ አስር ቤቶች ታድሰው ለተጠቃሚዎች ዛሬ ርክክብ ተደርጓል።
ለቤቶቹ ግንባታ፣ ለቤት መገልገያ ቁሳቁስና ለተጠቃሚ ቤተሰቦች አልባሳት ግዢ በጥቅሉ ከ2.1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደጓልም ብለዋል አቶ ተካልኝ። ቤቶቹን በመገንባት ስራ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሙያ የተሳተፉ የዩኒቨርሲቲው መምህራንም በእለቱ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
ችሮታው አየለ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት፤ በርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ባደረጉት ንግግር፤ ፍትህ እንዳይጓደል ዩኒቨርሲቲው ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በዲላ ከተማ፣ ወናጎ፣ ቡሌ፣ ይርጋጨፌ፣ ጨለለቅቱ፣ ገደብ እንዲሁም አባያ ወረዳ ነፃ የሕግ አገልግሎት እየሰጠ መቆየቱን ገልፀዋል።
ይህን አገልግሎት አጠናክሮ ለመቀጠል በፍርድ ቤቶች አካባቢ ቢሮዎችን መገንባት አስፈላጊ ሁኖ በመገኘቱ፤ በዛሬው ዕለት የዲላና የወናጎ የአገልግሎት ማዕከላት ተመርቀው ወደ ስራ መግባታቸውን እንዲሁም የቀሩት በቀጣይ ተጠናቀውና የሰው ሀይል ተመድቦላቸው ወደ አገልግሎት እንደሚገቡ አክለው ተናግረዋል።
ፕሬዚደንቱ በምርምር የሚለማው ስነ-ህይወታዊ የአፈር ማዳበሪያ (ቨርሚ ኮምፖስት) አስመልክተው፤ የተፈጥሮአዊ የአፈር ለምነት መጠበቂያ ማዳበሪያ እንደ ሀገር ብሎም እንደ አካባቢ ያለውን የኬሚካል ማዳባሪያ እጥረትና የዋጋ ውድነት ለማቃለል አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
በሌላ በኩል፤ ለአቅመ ደካማ ቤቶችን መስራትና ማደስ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩትን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራ ዩኒቨርሲቲው እንደ አርአያ በመከተል በየዓመቱ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝና በዘንድሮው ዓመትም የአስር አቅመ ደካማ ዜጎች ቤቶች ታድሰው ርክክብ መደረጉን አስገንዝበዋል።
አቶ አብዮት ደምሴ፣ የጌዴኦ ዞን አስተዳዳሪና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ አባል በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦ፤ ማህበረሰቡ ከፍተኛ አድናቆት እንዳለው ገልጸው፤ ዩኒቨርሲቲው የጀመረውን ስራ አጠናክሮና አስፍቶ እንዲሰራ አስተዳደራቸው አስፈላጊውን እገዛ ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ቤታቸው ከታደሰላቸው ዜጎች መካከል አቶ አገዘ በደቻ የይርጋጨፌ ከተማ 02 ቀበሌ ነዋሪ እንዲሁም ወ/ሮ ሳዬ ዋሬ የወናጎ ወረዳ ባለቦቄሳ ቀበሌ ነዋሪ በሰጡን አስተያየት፤ ቤታቸው ጠባብ እና በእርጅና ምክንያት በክረምት ውሃና ብርድ እየገባ ያስቸግራቸው እንደነበር አስታውሰው፤ ይህን ተገንዝቦ ለችግራቸው በመድረስ ድጋፍ ላደረገላቸው ዲላ ዩኒቨርሲቲ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በምርቃትና ርክክብ ስነ-ስርዓቱ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አመራር አባላትን ጨምሮ፣ የጌዴኦ ዞን አስተዳደር፣ የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የአባያ ወረዳ አስተዳደር ፣ የወናጎ ወረዳ አስተዳደር እና የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ተወካዮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በመርሃ-ግብሩ ፕሮጀክቶችን በአግባቡ ለግብ እንዲደርሱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የምስጋናና እውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ