የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ተፈታኞችን ተቀብሎ ለመፈተን ዝግጅቶች መጠናቀቃቸው ተገለፀ

ዲ.ዩ፦ ሐምሌ 15/2015 ዓ.ም(ህ.ዓ.ግ)፦ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ተፈታኞችን ተቀብሎ ለማስፈተን ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጿል።
ችሮታው አየለ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት፤ እንደ ሀገር በተያዘው አቅጣጫ መሰረት ፈተናው በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱ ኩረጃና ማጭበርበርን ለማስቀረት ወሳኝ ነው ብለዋል።
ተማሪዎች ፈተናቸውን በራሳቸው ጥረትና አቅም እንዲሰሩ ለማድረግና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት አንድ አካል መሆኑንም ነው ፕሬዝዳንቱ ያስገነዘቡት። አያይዘውም፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድና የፈተና ሂደቱን በስኬት ለማጠናቀቅ ሙሉ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።
እንደ ፕሬዚደንቱ ገለፃ፤ ባለፈዉ አመት የታዩ ክፍተቶችን በማረምና የነበሩ ጠንካራ ልምዶችን በማስፋት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ተማሪዎችን ከመቀበል ጀምሮ ወደ ቤታቸው መሸኘት ድረስ ያለውን ሂደት በአግባቡ ለመወጣት በቂ ዝግጅት ተደርጓል።
ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መርሐ ግብር መሠረትም ዲላ ዩኒቨርሲቲ በሁለት ዙር ፈተና 16 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በኦዳያአ፣ ሐሴዴላና የቀድሞው ዋና ግቢ እንደሚያስተናግድ አሳውቀዋል።
ዶ/ር ችሮታው ለተፈታኞች መልካም እድልን ተመኝተው፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የፈተና ሂደቱ በሰላምና በውጤት ይጠናቀቅ ዘንድ ርብርብ እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ