የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ልዩ ልዩ ዳይሬክተሮች ጋር ተወያዩ

ዲ.ዩ፦ ግንቦት 26/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በዲላ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ዘርፍ ማህበረሰብ አባላት ጋር ተወያዩ።
ከትላትን ጀምሮ የመስክ ምልከታ በዲላ ዩኒቨርሲቲ እያካሄዱ ያሉት የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በዛሬው የከሰአት ውሏቸው ከአካዳሚክ ዘርፍ ዳይሬክተሮች፣ ኮሌጅ ዲኖች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች እና ከየትምህርት ክፍሎች ከተወጣጡ መምህራን ጋር ነው ውይይት ያደረጉት።
በውይይቱ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ከዩኒቨርሲቲው መምህራን ጋር ውይይት ማካሄድ ያስፈለገው በሀገሪቱ ቁልፍ ድርሻ ያለውን የተማረ የሰው ኃይል የሚፈጥሩ በመሆናቸው ነው ብለዋል።
በተለይም የትምህርት ጥራት፣ የዩኒቨርሲቲዎች የትኩረት ልየታ እና የራስ-ገዝነት ጉዳዮች፣ ለመማር ማስተማር ግብአት አቅርቦት፣ ችግር ፈቺ እና ህዝብን የሚጠቅም ምርምር የማካሄድ ስራ፣ የተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ዝግጅት፣ ባለፈው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የተገኙ ልምዶች እና የዚህ አመት ዝግጅት በመሳሰሉ ጉዳዮች ከዲላ ዩኒቨርሲቲ አንፃር ውይይት ተደርጎባቸዋል።
መምህራኑም በሀገሪቱ ባለው የተጓተተ እና ውስብስብ የግዥ ስርአት የተነሳ ለትምህርት ጥራት የሚያግዙ የግብአት አቅርቦት ፍላጎቶችን በተገቢው ጊዜና ቅልጥፍና ማሟላት አስቸጋሪ ሁኗል ብለዋል። ስለሆነም ዩኒቨርሲቲዎች የተሻለ ትምህርት ለመስጠትና ብቁ ዜጋ ለማፍራት በግብአት እጥረት እየተፈተኑ ነው ሲሉ ሀሳባቸውን ለቋሚ ኮሚቴው አካፍለዋል።
ምንም እንኳን እንደ ሀገር ያለው የኢኮኖሚ ጫና የሚታወቅ ቢሆንም የከፍተኛ ትምህርት መምህራኑን ኑሮ ለማሻሻል፣ የተረጋጋና ለምርምር የሚያተጋ፣ ለትምህርት ትኩረት የሰጠ ማሻሻያ እንደ ሀገር በትኩረት ቢሰራ በቀጥታ የትምህርት ጥራቱ ላይ አውንታዊ ሚና መጫዎት ይገባል ነው ያሉት መምህራኑ።
የዩኒቨርሲቲዎች የራስ-ገዝነት ትግበራም ዩኒቨርሲቲዎቹ ያሉበትን አካባቢያዊ ሁኔታ፣ ተቋማዊ አቅም፣ የሰው ኃይልና ቁሳዊ ሀብትንም በሚገባ ታሳቢ ቢደረግ መልካም ነው ብለዋል። አለበለዚያ ቀደም ብለው የተመሰረቱና በተሻለ ሁለንተናዊ አቅም ላይ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችን ብቻ ታሳቢ የተደረገ ትግበራ ውስጥ ከተገባ አዲሶቹን እና ከቦታ አንፃር ከማዕከል የራቁትን የበለጠ ያቀጭጫል ብለዋል።
ቋሚ ኮሚቴው ከአስተዳደር ዘርፉ ልዩ ልዩ የዳይሬክቶሬት ፅ/ቤት ኃላፊዎች ጋርም የተወያየ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው ስላሉ የስራ አተገባበር ሁኔታዎች፣ ተቋማዊ ቁመና እና መሻሻል ስለሚገባቸው ጉዳዮች ምክክር አድርጓል።
በዛሬው ውሎ ማጠቃለያም ከተማሪዎች ህብረት አባላት በትምህርት፣ በአገልግሎት፣ በፈተና ዝግጅት እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ውይይት አድርገዋል።
የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በዲላ ዩኒቨርሲቲ እያካሄዱት ያለውን ምልከታ ነገ ከሰአት በፊት የሚያጠናቅቁ ይሆናል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በመስክ ምልከታ እና በውይይቶቹ ልየታ ባካሄዱባቸው እና መፍትሄ በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ነገ ጠዋት ከዩኒቨርሲቲው የማኔጅመንት አባላት ጋር የማጠቃለያ ውይይት ያካሂዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ