የዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተመራማሪዎች በጣሊያን አገር ቱሪን ዩኒቨርሲቲ ጉብኝት አካሄዱ

ዲ.ዩ፦ ግንቦት 10/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፥ በዲላ ዩኒቨርሲቲ እና በጣሊያን አገር የሚገኘው ቱሪን ዩኒቨርሲቲ የጋራ ትብብር ስምምነት አካል የሆነ የመምህራን ጉብኝት ተካሄደ። የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሶስት መምህራንና ተመራማሪዎች ናቸው ከሚያዚያ 28 እስከ ግንቦት 11/2015 ዓ.ም የሚቆየውን ጉብኝት በቱሪን ዩኒቨርሲቲ እያካሄዱ ያሉት።
እንደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የዲላ ዩኒቨርሲቲ በተሰጡት ተልዕኮዎች ውጤታማ ለመሆን አገራዊና ዓለምአቀፋዊ ትብብሮችን ከተለያዩ ተቋማት ጋር እየተፈራረመ ይተገብራል። በጣሊያን አገር ቱሪን ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ያለው የመምህራኑና ተመራማሪዎቹ ጉብኝትና ወይይትም የዚሁ አላማ አካል መሆኑ ነው የተገለፀው።
ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች በ2012 ዓ.ም በተፈራረሙት የጋራ ስምምነት መሰረት ከ"ኢረስመስ" የዝውውር ፈንድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የመምህራን እና የተማሪዎች ልውውጥ ለማካሄድ ስምምነት አላቸው፡፡
በስምምነቱ መሰረት ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ሶስት መምህራንና ተመራማሪዎች ማለትም የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ተወካይ ደረጀ ክፍሌ (ዶ/ር)፣ የሀገረሰብ ጥናት ተቋም ዋና ኃላፊው አቶ ተስፋጽዮን ጴጥሮስ፣ እንዲሁም ኦንጋዬ ኦዳ (ዶ/ር) ናቸው በቱሪን ዩኒቨርሲቲ ውይይትና ጉብኝት እያካሄዱ ያሉት።
መምህራኑና ተመራማሪዎቹ በቱሪን ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ጥናታዊ ጽሑፎችን ያቀረቡ እና የዲላ ዩኒቨርሲቲን እና የሀገረሰብ ጥናት ተቋምን የአካዳሚክና የምርምር ስራዎችን ያስተዋወቁ ሲሆን፥ የተጀመረው የሁለትዮሽ ትብብር የሚጠናከርበት፣ የሚሰፋበትና ዘላቂ የሚሆንበት ሁኔታ ላይም ምክክሮችን አካሂደዋል፡፡
በቆይታቸው በነበሩ ሁለት መድረኮች የቱሪን ዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ተጋባዥ ተመራማሪዎች እና የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች በታደሙበት ጉባኤ ሶስት የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎችን አቅርበዋል፡፡ ከቱሪን ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች ጋርም በሁለትዮሽ ትብብሮች ዙሪያ ውጤታማ ውይይት ማካሄዳቸውንም ደረጄ ክፍሌ (ዶ/ር) የላኩልን መረጃ ያመላክታል።
በመረጃው እንደተመላከተው መምህራኑና ተመራማሪዎቹ በቱሪን ዩኒቨርሲቲ በነበራቸው ቆይታ ከጉብኝትና ምክክሮቹ ባሻገር በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ሆነው በተማሪዎች ልውውጥ መርሀ-ግብር ወደ ቱሪን ዩኒቨርሲቲ ለስድስት ወራት ለትምህርት ከሄዱ ተማሪዎች ጋርም ውይይት መካሄዱ ተገልጿል።
የቱሪን ዩኒቨርሲቲ በጣሊያን አገር ከሚገኙ አንጋፋ የትምህርት ተቋማት አንዱ ሲሆን ከዛሬ 600 ዓመታት በፊት እ.አ.አ በ1404 ዓ.ም እንደተመሰረተ የዩኒቨርሲቲው የታሪክ ማህደር ያስረዳል።
..................
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ