ለጌዴኦ ዞን ግብርና ባለሙያዎች በ"ጂ.አይ.ኤስ" የመረጃ አሰባሰብ ዙሪያ የክህሎት ማጎልበቻ ስልጠና ተሰጠ

ዲ.ዩ፦ ግንቦት 10/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ከጌዴኦ ዞን ጋር በመተባበር በ"ጂ.አይ.ኤስ" (GIS) አጠቃላይ ዲጂታል መረጃ አሰባሰብ ዙሪያ ለዲላ ዙርያ ወረዳ 17 የግብርና ባለሙያዎች የክህሎት ማጎልበቻ ስልጠና ተሰጥቷል።
በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አለማየሁ አካሉ (ዶ/ር)፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ኘሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ፤ ለምንሰራው ስራ በቂ ክህሎትና እውቀት መታጠቅ በእጅጉ አስፈላጊ በመሆኑ፤ ያለንን እና የጎደለንን ለመለየት ይህ ስልጠና ትልቅ አስተዋጾ አለው ብለዋል።
ዶ/ር አለማየሁ አክለው፣ ኘሮጀክቱ ጌዴኦ ዞን ምን ሀብት እንዳለው፣ ያለውን ሀብት እንዴት መጠቀም እንደሚችል፤ በለየ አኳኋን መረጃን በደንብ አደራጅቶና ሰንዶ ለመያዝ ጉልህ ሚና ይኖረዋልም ብለዋል።
በቀጣይ እንደ ዞን ለሚሰሩ ስራዎች አስፈላጊ የሆኑ እቅዶችን ለማቀድ፣ ውሳኔዎችን ለመወሰን፣ የሚጠቅም መረጃ ለመሰብሰብ ብሎም ለማደራጀትና መልሶ ለመጠቀም እንዲሁም ታሳቢ ተደርጎ የሚሰራ ስራ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
አሁን ያለንበት ዘመን የመረጃ ዘመን እንደመሆኑ መጠን፤ ለምንሰራው ስራ መረጃ አቅም የሚሆነው ደግሞ በአግባቡ ሲጠናቀርና ሲተነተን ብቻ በመሆኑ በዚህ አግባብ ሊሰራ እንደሚገባ ዶ/ር አለማየሁ ተናግረዋል።
ብርሃኔ ገ/ህይወት (ዶ/ር)፣ በዲላ ዩኒቨርስቲ የግብርና እና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የ"Geospatial" ፕሮጀክት ቡድን መሪ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ ከተጀመረ አንድ አመት መሆኑን ገልፀው፤ እስካሁን ድረስ የተለያዩ ዝግጅቶች ሲያካሂድ መቆየቱን ገልፀዋል።
ዶ/ር ብርሃኔ አያይዘውም፤ በአሁኑ ሰዓት በጌዴኦ ዞን ካሉ ወረዳዎች የመጀመሪያ የዲላ ዙርያ ወረዳ የግብርና ባለሙያዎችን " Web-based" የመረጃ አሰባሰብ ዘዴዎችን ከወረዳው ለተወጣጡ 17 የግብርና ባለሙያዎች መሰጠቱን ገልጸዋል።
ስልጠው በ"ኦንላይን" የሚከወን የመረጃ አሰባሰብ ስርአትን የሚተገብርና ከወረቀት የፀዳ ከመሆኑ በላይ ትክክለኛና ተዓማኒ እንዲሆን ታቅዶ እየተሰጠ መሆኑንም አንስተዋል። እንደ ዶ/ር ብርሃኔ ገለጻ፣ መረጃዎችን እንዴት በ"ታቢሌት" መመዝገብ እንደሚቻል ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ነውም ብለዋል።
አቶ ዳንኤል ሽፈራው፣ የጌዴኦ ዞን ኘላን ልማት መምሪያ ኃላፊ እና በዞኑ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ በአንፃሩ፤ የኘሮጀክቱ እንቅስቃሴ የተጀመረው ከዛሬ 12 ዓመት በፊት በ2003 ዓ/ም እንደነበር ገልፀው፤ በተለያዩ ምክንያቶች ኘሮጀክቱ በተፈለገው ልክ አለመሄዱን አስታውሰዋል።
ሆኖም የጌዴኦ ዞን ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በ2014 ዓ/ም በአዲስ መልኩ የውል ስምምነት በመፈራረም ወደ ትግበራ መግባቱን አስገንዝበዋል።
ኘሮጀክቱ በሦስት አመታት የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ የተመደበለት ገንዘብ 13 ሚሊየን 694 ሺህ 361 ብር እንደሆነ አቶ ዳንኤል ተናግረዋል።
ኘሮጀክቱ በታለመለትና በታቀደው መሰረት መረጃው ተሰብስቦና ተሰንዶ ሲያዝ፤ በዞኑ ያሉ አቅሞችም ውስንነቶችም ተለይተው ስለሚቀመጡ ለተመራማሪም ሆነ ድጋፍ ለሚያደርጉ አካላት ስራን የሚያቀል ይሆናል ተብሏል።
ሰልጠናውን ሲሳተፉ ካገኘናቸው ባለሙያዎች መካከል፤ ተገኝ ኤፍሬም፣ ምችሌ ሆላና እና ዮሴፍ አለማየሁ ሥልጠናው በቀጣይ ለሚሰሩት ስራ ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጾ እንዳለው ገልፀው፣ በዞኑ ያለውን የመረጃ አያያዝ ከማዘመኑ በላይ ዞኑ ያለውን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም እገዛው የጎላ ይሆናል ሲሉ ሐሳባቸውን አጋርተውናል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ