የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በዲላ ዩኒቨርሲቲ ያካሄዱትን የስራ ጉብኝት አጠናቀቁ

ዲ.ዩ፦ ግንቦት 27/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ የስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በዲላ ዩኒቨርሲቲ ሲያካሂዱት የነበረውን የስራ ጉብኝት ማጠቃለያ መድረክ ዛሬ አካሂደዋል።
በጉብኝቱ በበጀት ዓመቱ የመማር ማስተማር፣ ጥናትና ምርምር፣ ማሕበረሰብ አገልግሎት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የተመራቂ ተማሪዎች መውጫ ፈተና ዝግጅት እና የመሳሰሉትን ስራዎች የገመገሙ ሲሆን የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በዩኒቨርሲቲው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችንም ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
እንዲሁም ከመምህራን፣ ተማሪዎች እና አስተዳደር ዘርፍ የስራ ኃላፊዎች ጋር ያካሄዷቸውን ውይይቶች መቋጫ በዛሬው ዕለት ከዩኒቨርሲቲው ማኔጀመንት ጋር የማጠቃለያ ውይይት መድረክ በማካሄድ አጠናቀዋል።
ከማኔጅመንት አባላት ጋር በተካሄደው የመውጫ ውይይት የቋሚ ኮሚቴው አባላት በመስክ ምልከታዎች እና ውይይቶች የተገኙ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ለይተው አቅርበዋል።
ዩኒቨርሲቲው መሪ ቃሉን በተግባር መተርጎሙ፣ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጋፍ ማዕከል ማደራጀቱ፤ ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት መስጠቱ፣ በምርምር ስራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገት ማሳየቱ፣ በተለያዩ ዘርፎች ለአካባቢው ማሕበረሰብ ተደራሽ አገልግሎቶች መሰጠቱ ጥንካሬዎቹ ናቸው ብለዋል።
በተጨማሪም የውስጥ ገቢ ለማመንጨት ብሎም ራሱን ለመቻል ጥረት መጀመሩ፤ በተለይም የዶሮ እርባታ፣ የወተት ከብት እርባታ፣ እፅዋት ጥበቃና ኢኮቱሪዝም ማዕከል ልማት ስራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸውም ብሏል ቋሚ ኮሚቴው።
የዜሮ ፕላን ፕሮግራም እንቅስቃሴዎች፣ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራን በስኬት ማከናወን መቻሉ፣ ያረጁ ህንፃዎች በአግባቡ መታደሳቸው በመስክ ምልከታዎቹ የተመለከትናቸው ከዩኒቨርሲቲው ስራዎች በጥንካሬ የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ።
በአንፃሩ በአመራር ደረጃ የሴቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆን፣ አንድ አንድ የትምህርት አይነቶች በአግባቡ አለመጠናቀቃቸው፣ የመምህራን መኖሪያ ችግር አለመቀረፍ፣ የትራንስፖርት እና መኪና ችግር፣ የሰራተኞች የስራ ተነሳሽነት ዝቅተኛ መሆን፣ የጤና እና ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ የሐኪሞችና መምህራን የትርፍ ሰዓት ክፍያ መዘግየት መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።
በማጠቃለያ መድረኩ በተነሱ ነጥቦች ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት ችሮታው አየለ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት፤ እንደ ክፍተት የተለዩት ጉዳዮች በቀጣይ በእቅድ ተይዘውና ተስተካክለው እንዲሁም ጠንካራ ጎኖች በይበልጥ ጎልብተው እንዲወጡ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ዶ/ር ችሮታው አያይዘው፤ የተማሪዎች የምግብ ፍጆታ በጀት እጅግ አናሳ መሆን ቁርስ፣ ምሳ እና እራት ለማቅረብ ከፍተኛ ችግር እንደሆነ ጠቁመዋል። ይህ በመንግስት ደረጃ የተመደበው አነስተኛ በጀት በአሁኑ ነባራዊ ሁኔታ ተማሪ ለመመገብ በቂ አለመሆኑን ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው በከፍተኛ የበጀት ጫና ተጨማሪ ወጪ እያወጣ ነው ተማሪ የሚመግበው ብለዋል። ይህ በመንግስት ዘንድ ትኩረት ተሰጥቶት መፈታት ያለበት ጉዳይ ነው ብለዋል።
የትምህርት ግብዓት ለማሟላት እናና የትራንስፖርት መኪና ለመግዛት የግዥ ስርዓቱ ማነቆ መሆኑን፤ የጤና እና ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ የመማር ማስተማርና ሕክምና አገልግሎት ያለውን ክፍተት የሚመነጨው ከበጀት አመዳደብ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዩኒቨርሲቲው የሚበጀተው በጀት የትምህርት ስራውን ለማከናወን እንጅ የህክምና ዘርፉን የተመለከተ በጀት እንዳልሆነ አስረድተዋል። ይሁን እንጅ የህክምና አገልግሎቱ መቀጠል ስላለበት ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ የበጀት ጫና ውስጥም ሆኖ በእራሱ ጥረት እየሸፈነ ነው።
ይሁን እንጅ ከዚህ ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ከትምህርት ሚኒስቴር እና ጤና ሚኒስቴር ጋር ባለ ግንኙነት ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ቋሚ ኮሚቴውም የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ የስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የትምህርት ስራ ሀገር የሚረከብ ትውልድ በዕውቀት፣ በክህሎትና በጥሩ ስነ-ምግባር የመቅረጽና ማፍራት ትልቅ ስራ መሆኑን በአፅንኦት ገልፀዋል።
የተከበሩ ዶ/ር ነገሪ አክለውም እንደ ሀገር የውስጥና የውጭ ጫናዎችን ተቋቁመን ትልቁን፣ ምስል በማየት በእጃችን ያለውን አቅም ተጠቅመን የተሰጠንን ተልዕኮ ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ አመራር ለስራ ያለውን ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት የሚያበረታታ ነው ያሉት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ዶ/ር ነገሪ፣ ተቋሙ ያለውን የሰው እና ልዩ ልዩ ሃብት በመጠቀም ራሱን ለመቻል፣ የአካባቢውን ማሕበረሰብ ለመጥቀም፥ በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በምርምርና ቴክኖሎጂ ፈጠራና ሽግግር፣ በግብርና፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ቱሪዝም እንዲሁም በአገርና ዓለምአቀፍ ጉድኝት ፕሮጀክቶችን በመቅረጽና በመስራት ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።
ዶ/ር ነገሪ አክለውም፤ ቋሚ ኮሚቴው ከሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የምክር ቤት አባላት እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማነቆ የሆኑት ሕግ እና ደንቦች እንዲሁም መመሪያዎችን ለማሻሻል በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ