የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ውይይት ተካሄደ

ዲ.ዩ፦ ግንቦት 24/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል ጉባዔ በዩኒቨርሲቲው የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ዛሬ ውይይት አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ በተለያዩ ዘርፎች የተከናወኑ የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸሞች ለመድረኩ ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
በእለቱ ቅድሚያውን ወስደው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ታምራት በየነ (ዶ/ር) በዘርፉ የተከናወኑ ስራዎችን ሪፖርት አቅርበዋል። በሪፖርታቸው፤ በአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ስር ባሉ ክፍሎች በዘጠኝ ወራት የተከናወኑ ተግባራትን በየንዑስ ዘርፎች ቀንብበው አቅርበዋል።
ዶ/ር ታምራት በሪፖርታቸው ካነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል፤ በበጀት ዓመቱ የዘጠኝ ወራት አዳዲስ የትምህርት መስኮች ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ መከፈት፣ ለመምህራን በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የትምህርት ዕድሎች መሰጠቱን፣ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በስራ ላይ አጫጭር ስልጠናዎች መሰጠቱን፣ እንዲሁም ለመማር ማስተማር የሚያገለግሉ ግብአቶች ለማሟላት ጥረት መደረጉን አብራርተዋል።
በሪፖርቱ፤ የሴት ተማሪዎችን አቅም ለማሻሻል የማጠናከሪያ ትምህርት መሰጠቱ፣ የአካቶ (Inclusiveness) መማር ተግባራዊ ለማድረግ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ስልጠና መሰጠቱን፣ የህግና ህክምና ተማሪዎች አገር አቀፍ መውጫ ፈተና ተፈትነው ጥሩ ውጤት መመዝገቡ የተሻሉ አፈፃፀሞች መሆናቸው ተነስቷል።
በዚህ ዓመት ለሚጀመረው የተመራቂ ተማሪዎች አገር አቀፍ የመውጫ ፈተና ዝግጅት መደረጉንና የመጀመሪያ ዙር የሞዴል ፈተና በ"ኦንላይን" የፈተና አስተዳደር ስርአት ለተማሪዎች መሰጠቱን፣ ሁለተኛ ዙር የሞዴል ፈተና ለመስጠት ዝግጅት መደረጉንም ዶ/ር ታምራት አንስተዋል።
የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር ታምራት አክለውም በበጀት ዓመቱ ከዚህ ቀደም ትምህርታቸውን ላጠናቀቁ ተማሪዎች ጊዚያዊ ውጤት (Temporary)፣ ዋና (Official)፣ ኦፊሻል ትራንስክሪፕትና ሌሎች አስፈላጊ የትምህርት መረጃዎችን የመስጠት ስራ መከናወኑን አንስተዋል።
********
በተመሳሳይ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ የዘጠኝ ወራት ሪፖርትን ያቀረቡት ደግሞ የዘርፉ ምክትል ፕሬዝዳንት ሀብታሙ ተመስገን (ዶ/ር) ናቸው። በሪፖርታቸው ለጥናትና ምርምር የሚውሉ ፕሮፖዛሎች ተቀብሎ በማጽደቅ፣ ተሰርተውና ታትመው ወደ ተግባር እንዲውሉ መደረጉን ዶ/ር ሀብታሙ አንስተዋል።
ዶ/ር ሀብታሙ በሪፖርታቸው፤ የሁለተኛ እና የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በመደገፍ በምርምር ስራ እንዲሳተፉ መደረጉን፣ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች፣ ዎርክሾፕ፣ ሴሚናሮች፣ የሳይንስ ሳምንት ሁነቶች፣ እንዲሁም ለሴት መምህራንና ተመራማሪዎች በምርምር የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
ከአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጉድኝነት ፕሮጀክቶች መሰራታቸውን፣ ለአካባቢው ማህበረሰብ በተደራሽ ፕሮጀክት ቡና፣ እንሰት፣ አፕል፣ ማንጎ እና ሌሎች በምርምር የለሙና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ችግኞች መሰራጨታቸውን አቅርበዋል።
ሪፖርቱ አያይዞም፣ ለሕብረተሰቡ ህይወት መሻሻል የሚጠቅሙ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን፣ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ላላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ነፃ የህግ ምክር አገልግሎት መሰጠቱን፣ በዕፅዋት ጥበቃና ኢኮቱሪዝም ማዕከል ለአካባቢው ማሕበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ የመዝናኛና መናፈሻ አገልግሎት መሰጠት መጀመሩን ዳስሷል።
ዶ/ር ሁብታሙ አክለውም፤ የ"ቨርሚ ኮምፖስት" በማዘጋጀት ከ60 ኩንታል በላይ ለአርሶ አደሮች መከፋፈሉን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን ለማድረግ ከተለያዩ ኢንዱስትሪዎች እና ኢንተርፕራይዞች ጋር ትስስር የመፍጠር ስራ መሰራቱን፣ እንዲሁም በ"ስቴምሀ" ማዕከል ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች በማሰልጠን በአገር አቀፍ ደረጃ ተወዳድረው በጥሩ ውጤት ሶስተኛ ደረጃ ማስመዝገብ መቻሉን አቅርበዋል።
**********
የቢዝነስ እና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዮናስ ሰንደባ (ዶ/ር) በበኩላቸው ባለፉት ዘጠኝ ወራት በዘርፉ የተሰሩ ቁልፍ ተግባራትን አቅርበዋል። በሪፖርቱ፤ አዲስና ነባር ሜጋ ፕሮጀክቶች ስራቸው የተሳካ እንዲሆን ክትትልና ድጋፍ መደረጉን፣ በዩኒቨርሲቲው የታቀዱ መካከለኛና አንስተኛ ግንባታዎችን አጠናቆ ወደ ስራ ማስገባቱን፣ የዩኒቨርሲቲው ዘመናዊ የመረጃ ቋት (ዳታ-ቤዝ) የመዘርጋት ስራ መከናወኑን እንዲሁም የውሃና መብራት አቅርቦትን ለመሻሻል ጥረት መደረጉን አንስተዋል።
ዶ/ር ዮናስ ሪፖርታቸውን ሲቀጥሉ፤ የፍሳሽ ቆሻሻ የማከም ስራ መከናወኑን፣ የተማሪዎች የበር እና የመስኮት ብልሽት የማስተካከል ስራ መሰራቱን በተጨማሪም የውስጥ ገቢ ማመንጨት መጀመሩን እና ያልተጀመረ ክፍል ለማስጀመር የሚያግዙ ሰነዶች መዘጋጀታቸውን አንስተዋል።
**********
የአስተዳደር እና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ተወካይ አስናቀ ሙሉዬ (ዶ/ር)፣ በዘርፉ በአጠቃላይ የተከናወኑ ስራዎችን አቅርበዋል።
ሪፖርታቸውን፤ የዩኒቨርሲቲውን ዓላማ ለማሳካት የድጋፍ ሰጪ ዘርፎች እየሰሩ እንደሚገኙ በመግለጽ የጀመሩት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ በተለይ አሁን ዩኒቨርሲቲው ከተመደበበት "አፕላይድ ሳይንስ" ዘርፍ አንፃር ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀስ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል። በባህሪው የአፕላይድ ሳይንስ የትኩረት አቅጣጫ ተግባር ተኮር ስለሆነ በዚያ ዘርፍ ላይ እየተሰራ መሆኑን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
በፋይናንስና በጀት ስር ምቹና ቀልጣፋ በጀትን መሠረት ያደረገ፣ አግባብ ያለው የክፍያ ስርዓት እንዲኖር እንዲሁም የመንግስትን መመሪያ የተከተለ የፋይናንስና አገልግሎት እንዲኖር ማስቻል መሆኑን ጠቅሰው፤ በተቋሙ ውስጥ የማመቻቸትና ድጋፍ የመስጠት ስራ እንደተሰራ አንስተዋል።
ክፍያዎችን ሁሉ በኦንላየበኦንላይን ባንኪንግ ስርአት መፈፀም መቻሉን ይህም የክፍያ ስርአቱን እንዳሻሻለው ጠቅሰዋል። ይሁን እንጅ ከግብአት አቅርቦት ግዥዎች አንፃር አሁንም የተጓተተ የግዥ ስርአት ማነቆ ነው ብለዋል ዶ/ር አስናቀ።
***********
በእለቱ ሌላው የዘጠኝ ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት፣ የህክምና እና ጤና ሳንስና ኮሌጅ አጠቃላይ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ ተወካይ ዶ/ር ዘሪሁን ተስፋዬ፤ አጠቃላይ ሆስፒታሉ መማር ማስተማር ስራውን ከጀመረ ወዲህ አሁን 18 የትምህርት መርሃግብሮች እና 1033 ተማሪዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ዶ/ር ዘሪሁን በሪፖርታቸው፤ ሆስፒታሉ እድሜ ጠገብ ከመሆኑ እና ከነበሩበት ዘርፈ ብዙ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶ አንፃር ትኩረት የሚሻ ሆኖ የመልሶ ማደስ ስራዎች እየተሰሩለት ነው ብለዋል።
ዶ/ር ዘሪሁን በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ በጤና ሚኒስቴር ለውጥ ያሻቸዋል ተብለው ከተተኮረባቸው ሆስፒታሎች አንዱ ከሆነ ጊዜ ጀምሮ በመርሃግብሩ የተቀመጡ መለኪያዎችን ለማሟላት በተሰራው ጠንካራ ስራ አሁን ላይ የተሻሉ ከሚባሉት ውስጥ ደረጃ ይዟል ብለዋል።
ምንም እንኳን የአዲሱ ሆስፒታል ህንፃ ግንባታ መዘግየት የተሻለ ቁመና ላይ ለመገኘት እንከን ቢሆንም በአንፃሩ በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር በተወሰደው ቁርጠኛ ውሳኔ መሰረት በነባሩ ሆስፒታል ላይ በጣናት ተመስርቶ እየተካሄደ ያለው የመልሶ ማደስ ግንባታ ችግሮችን እየቀረፈ ነው ብለዋል ዶ/ር ዘሪሁን።
***********
ለፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ተጠሪ በሆኑ ዳይሬክቶሬቶችና ፅ/ቤቶች የተከናወኑ ሪፖርቶችን አቶ አበባው ካሴ ያቀረቡ ሲሆን፤ ከትምህርት ሚኒስቴር ለመጡ ባለድርሳዎች ከአራቱም ግቢ ኃላፊዎች አስተዳደር ዕቅዳቸውን ሰርተው እንዲያቀርቡ መደረጉን፣ የስራ ክፍሎች የበጀት ድልድል ተደርጎ በ2015 በጀት ዓመት ከገንዘብ ሚኒስቴር ለፕሮግራሞች መፈቀዱንና በወጣው ጣሪያ መሠረት ለስራ ክፍሎች የበጀት ድልድል መደረጉን፣ እንዲሁም ፊስካልና ፋይናንስ ዕቅድ አጠቃቀም ሪፖርት ለሚመለከታቸው ክፍሎች መተላለፉ በሪፖርቱ አካተዋል።
ልዩ ልዩ ዩኒቨርሲቲው የስራ እንቅስቃሴዎች፣ ጉባኤዎች፣ ፕሮጀክቶች እና መሰል ተግባራትን በሚዲያ ሽፋን በማሰጠት ለህዝብ የመረጃ ፍላጎት ተደራሽ ተደርጓል ብለዋል። እንዲሁም ልዩ ልዩ የህግና የአስተዳደር ጉዳዮችን በህግ አገልግሎት በኩል አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት አቶ አበባው በሪፖርታቸው።
***********
ሪፖርቶቹ ከቀረቡ በኋላ ከካውንስል አባላት የተለያዩ ሐሳቦች፣ ጥያቄዎች እንዲሁም ገንቢ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። ትኩረት ተደርገው ከተነሱ ጉዳዮች መካከል፤ የኮርስ ባለቤትነት ጉዳይ፣ የትምህርት ግብዓቶች በሚፈለገው ልክና አግባብ አለመሟላት፣ የመምህራን መኖሪያ ቤት ግንባታ መጓተት እና የቤት አበል ክፍያ መዘግየት፣ የተማሪዎች የመስክ ጉዞ ፣ የትራንስፖርት ችግር፣ የስራ ክፍሎች ተናቦ የመስራት ክፍተቶች እና ሌሎችም ሐሳቦች ተነስተዋል።
በተነሱት ሐሳብ አስተያየት እንዲሁም ጥያቄዎች ዙሪያ ከየዘርፍ ሐላፊዎች ምላሽ ከተሰጠባቸው በኋላ ዶ/ር ችሮታው አየለ፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ለካውንስል አባላት መሰረታዊ ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገዋል።
ዶ/ር ችሮታው በገለጻቸው፤ የሀገራችንና ተቋማችን ተጨባጭ ሁኔታ በመገንዘብ በእጃችን ላይ ያለውን ሀብት ቅድሚያ መሥጠት እንደሚገባን በመለየት በአግባቡ በመጠቀም የተሰጠንን ተልእኮ በብቃት በወጣት አልብን ሲሉ አንስተዋል።
ፕሬዝዳንቱ በማጠቃለያ ማብራሪያቸው በዋናነት በተቋም አቅም ሊፈቱ የሚችሉ እና ጊዜ የማይሰጡ ጉዳዮችን የሚመለከታቸው ክፍሎች በትኩረትና በቅንጅት እንዲሰሩ መመሪያ ሰጥተዋል።
ከልዩ ልዩ ግንባታዎች መጓተት ጋር በተያያዘ የተነሳው ችግር በዋናነት እንደ ሀገር ካለው የኢኮኖሚ ጫና እንዲሁም የግንባታ ግብአቶች ዋጋ ማሻቀብ ጋር ተያይዞ የተቋራጮች የመፈፀም አቅም ደካማ በመምጣቱ ነውም ብለዋል።
ስለሆነም ከመንግስት ከፍተኛ አመራሮችና የሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር እየተነጋገርን ችግሮችን እየፈታን ለመጓዝ እየጣርን ነው ብለዋል። ይሁን እንጅ በአንዳንድ የግንባታ ፕሮጀክቶች ከአቅም በላይ የሆነው የኢኮኖሚ ቀውስ በተሻለ ለመስራት አላስቻለም ያሉ ሲሆን በዚያው መጠን ውል አቋርጦ ለተሻለ ተቋራጭ ስራ መስጠትም ካለው ውስብስብ አሰራርና ከሚመጣው የዋጋ መናር ጋር ተያይዞ ነገሮች ቀላል አልሆኑም ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።
ስለሆነም እንደ ሀገር ያለው የኢኮኖሚ ጫና በሚቀጥለው 2016 በጀታችንም ላይ ከፍተኛ ቅናሽ እንዲኖር አድርጓል ያሉት ዶ/ር ችሮታው ከወዲሁ ክፍሎች የማይቀሩና የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ተግባራት በአግባቡ እያቀዱ፣ በአግባቡ መፈፀም እንዳለባቸውም አቅጣጫ ሰጥተዋል።
ስለሆነም በሚቀጥለው ዓመት በተለይ የመማር ማስተማር ስራውን ለማሳለጥ፣ የትምህርት ጥራቱን በትኩረት ለማሳደግ፣ ተማሪዎችን በአግባቡ ለማብቃት የግብአት ማሟላት እና በዘርፉ ያሉ ችግሮችን መፍታት ቅድሚያ የሚሰጠው ስራ ነው ብለዋል።
የምርምር ስራዎቻችንም የተመጠኑ፣ ከፍተኛ ውድድር የሚኖርባቸው፣ ከዓለምአቀፍና ሀገር አቀፍ ትብብሮችን የሚፈጥሩ፣ ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ይሰራል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ። ስለሆነም ሁሉም የስራ ክፍል እንደ ሀገርና ተቋም ያለውን የበጀት ጫና በመረዳት በልዩ ትጋትና ትኩረት መስራት ይኖርብናል ሲሉ ማብራሪያቸውን ቋጭተዋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ