ዲላ ዩኒቨርሲቲ ከ "ኢንፎ ማይንድ ሶሉሽንስ" ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ

ዲ.ዩ፦ ግንቦት 11/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ ዲላ ዩኒቨርሲቲ "ኢንፎ ማይንድ ሶሉሽንስ" ከተባለ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር በተመራቂ ተማሪዎች ዙሪያ አብሮ ለመስራት የሚያስችል የስምምነት ሰነድ መፈራረሙ ተገልጿል።
ማቴዎስ ሀብቴ (ዶ/ር )፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ተወካይ፤ የተጠቀሰው ድርጅት በተመራቂ ተማሪዎች ዙሪያ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ለመስራት የውል ስምምነት ላይ መድረሱን ነው የገለፁት።
ድርጅቱ በተለይም ከ"ኢትዬ ጆብስ" (ከኢትዮጵያ ስራዎች) ማኅበር ጋር በመተባበር ለተመራቂ ተማሪዎች የተለያዩ ስልጠናዎችን እየሰጠ ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር በመስራት ለምሩቃን በስፋት እድሎችን እየፈጠረ እንደሚገኝ ተገልጿል።
እንደ ዶ/ር ማቴዎስ ሀብቴ ገለፃ፤ ድርጅቱ ከዩኒቨርሲቲው የ2015 ዓ.ም ተመራቂዎች መካከል በውጤታቸው አብላጫ ያመጡ 20 ተማሪዎችን ተቀብሎ ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር በማገናኘት ወደ ስራ ለማስገባት እና ዲላ ዩኒቨርሲቲን የማስተዋወቅ ስራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።
በዚህም ስምምነቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር በመውረድ ድርጅቱ በ"ደረጃ ዶት ኮም" ድህረ ገፅ አጠቃቀም እና በደረጃ አካዳሚክ አስተዳደር ዙሪያ ላይ የክህሎት ማበልጸጊያ ስልጠና በቅርቡ ለዲላ ዩኒቨርሲቲ የ2015 ዓ.ም ተመራቂ ተማሪዎች የሚሰጥ ይሆናል።
እነዚህ ስልጠናዎች ተመራቂ ተማሪዎች በስራ ፍለጋ ወቅት እውቀትና ክህሎት ኖሯቸው በመደናገጥና በመፍራት ብቻ ቃለ መጠይቁን ሳያልፉ ቀርተው ስራ የማያገኙበት ሁኔታ እንዳይፈጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል።
ዶ/ር ማቴዎስ አክለውም የስምምነት ሰነዱ የጊዜ ገደብ ሳይኖረው ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን እስካስመረቀ ድርስ ስምምነቱ በየአመቱ የሚቀጥል እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህ የመግባቢያ ስምምነት ለመነሻ ያህል ዘንድሮ በ20 ተመራቂ ተማሪዎች ይጀመር እንጂ፤ ወደፊት ዩኒቨርሲቲው ከድርጅቱ ጋር በሚያደርገው ግንኙነት እና በሚሰራቸው ስራዎች ቁጥሩ በየአመቱ ከፍ እያለ መጨረሻ ላይ ሙሉ ለሙሉ ተማሪዎችን የማስቀጠሩ ሂደት የሚፈጠርበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ዶ/ር ማቴዎስ አያይዘው ተናግረዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች ከምረቃ በኋላ ከስራ ፍለጋ ጋር ተያይዞ የሚገጥሟቸውን በርካታ ችግሮች ለመቅረፍ በድርጅቱ በቅርቡ የሚሰጡ ስልጠናዎች ስለሚኖሩ ተመራቂዎቹ ስልጠናዎችን ተነሳሽነት ኖሯቸው በስፋት እንዲሳተፉ ምክትል ፕሬዝዳንት ተወካዩ ከወዲሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ