
ዲ.ዩ፦ ሚያዚያ 13/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት በምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ አምስት ቀበሌዎች ለተውጣጡ አርሶ አደሮች በምርምር የለሙ የቡና ችግኞችን አሰራጭቷል።
ደረጀ ክፍሌ (ዶ/ር )፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት፤ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር እና ከምርምር ስራዎች ባለፈ በርከት ያሉ የማህበረሰብ ተደራሽ ፕሮጀክቶችን ለአካባቢው ህብረተሰብ ተጠቃሚነት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ከእነዚህ መካከል በዘንድሮ አመት በአባያ ወረዳ ሊሰራጭ ከታቀደው 42 ሺህ የቡና ችግኞች ውስጥ ለሚያዚያ ተከላ የደረሱ 36 ሺህ የቡና ችግኞች በዛሬው ዕለት ለአርሶ አደሮች መሰራጨታቸውን ነው ዶ/ር ደረጄ የገለፁት።
ዶ/ር ደረጄ አክለውም እነዚህ ምርትና ምርታማነታቸው የተረጋገጡ የምርጥ ዘር ዝርያዎችን አርሶ አደሩ የተሻለ ምርት ለማገኘት በአግባቡ እንክብካቤ እንዲያደርግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። አያይዘውም በቀጣይ የወረዳ አስተዳደሩ በሚለያቸው ችግሮች ዙሪያ ዩኒቨርሲቲው ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
አቶ ተካልኝ ታደሰ፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክተር በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ለዘንድሮ ዓመት በአራት የምርምር እና ሽግግር ማዕከላት ውስጥ 410 ሺህ የቡና ችግኖችን ለስርጭት አዘጋጅቷል ነው ያሉት።
ከእነዚህም ውስጥ በዛሬው ዕለት በአባያ ወረዳ የሰመሮ ችግኝ ጣቢያ ውስጥ 36 ሺህ የቡና ችግኖችን ለአርሶ አደሩ በማከፋፈል የስርጭት ስራው መጀመሩን አስታውቀዋል።
አያይዘውም ስርጭቱ በቀጣይ ቀናትም በኮቸሬ፣ በይርጋጨፌ እና ዲላ ዙሪያ ወረዳዎች ይቀጥላል ብለዋል። በምርምር የተገኙት እነዚህ የቡና ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች ማሰራጨት ምርታማነትን ከማሳደግ በላይ የአርሶ አደሩን ኑሮ ለመቀየር ትልቅ ፋይዳ አለው ነው ያሉት አቶ ተካልኝ።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የ'ሆርቲካልቸር' ትምህርት ክፍል መምህር እና የአባያ ወረዳ የሰመሮ ቡና ችግኝ ጣቢያ አስተባባሪ አቶ ፍቅሩ ታምሩ፤ የአካባቢው አርሶ አደሮች ከዚህ በፊት ዝርያው የማይታወቅ እና ምርታማነቱ ዝቅተኛ የሆነ ምርት ያመርት ስለነበር በሄክትር ከሰባት (7) ኩንታል በላይ ማምረት የማይቻል እንደነበር ገልጸዋል።
አሁን ላይ ግን ዩኒቨርሲቲው እነዚህን ውጤታማነታቸው የተረጋገጠ የቡና ዝርያዎችን አልምቶ ለአካባቢው ማህበረሰብ ማሰራጨቱ የአርሶ አደሮችን ምርት ከማሳደጉም በላይ ወደፊት ምርቱን ለውጪ ገብያ በማቅረብ ገቢ ለማሻሻል ይረዳቸዋል ብለዋል አቶ ፍቅሩ።
በሌላ በኩል አቶ መንግስቱ ብላዋ፣ የአባያ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ምርታማነታቸው የተረጋገጠ የቡና ችግኞችን ለአካባቢው አርሶአደሮች በስፋት ሲያሰራጭ መምጣቱን አስታውሰዋል።
የቡና ችግኝ ሲወስዱ ያገኘናቸው አርሶ አደሮች አቶ ፍቅሩ ቃልቻ እና አቶ ጌልጌላ ቱሪ በሰጡን አስተያየት፤ የቡና ችግኝ ስርጭቱ የአካባቢው ህብረተሰብ ከቡና ልማት የተሻለ ጥቅም እንዲያገኝ እንደሚያስችለው ገልጸውልናል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ