በጌዴኦ ዞን ኮቾሬ ወረዳ ለሚገኙ አርሶ አደሮች በምርምር የለማ የቡና ችግኝ ተሰራጨ

ዲ.ዩ፦ ሚያዝያ 15/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማሕበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት በጌዴኦ ዞን ኮቾሬ ወረዳ ከ19 ቀበሌዎች ለተውጣጡ አርሶ አደሮች በምርምር የለሙ የቡና ችግኞችን አከፋፍሏል።
ደረጀ ክፍሌ (ዶ/ር) በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት፤ ዩኒቨርሲቲው ከአስራ ሦሥት በላይ ለማህበረሰቡ ተደራሽ የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን እየሰራ ለማህበረሰብ ግልጋሎት ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
ከእነዚህም መካከል በዘንድሮ ዓመት በኮቾሬ ወረዳ ሊሰራጭ ከታቀደው 80 ሺህ የቡና ችግኝ ውስጥ ለሚያዚያ ተከላ የደረሱ 63 ሺህ የቡና ችግኞች ለአርሶ አደሮች እንዲደርሱ መደረጋቸውን ዶ/ር ደረጄ ገልጸዋል።
ዶ/ር ደረጄ አክለውም፤ የቡና ችግኝ ተደራሽ የተደረገላቸው አርሶ አደሮች የተመረጡት በቂ የሚያለሙበት ማሳ ያላቸው ሞዴል አርሶአደሮች፣ የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ለራሳቸው ከመጠቀም አልፈው ለአካባቢው ህብረተሰብ ማጋራት የሚችሉ፣ በኢኮኖሚ የአቅም ማነስ ምክንያት ችግኝ ገዝተው ለማልማት የሚቸገሩ፣ በወረዳው እና ቀበሌ አስተዳደር እንዲሁም በግብርና ባለሙያዎች ተመልምለው የቀረቡ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
እርሳቸው አያይዘውም፤ ለውጤታማነት ክትትል ይመች ዘንድ ችግኞች ተደራሽ የተደረገላቸው አርሶ አደሮች ለራሳቸው ብቻ እንዲያለሙ፣ ለሌላ ሰው አሳልፈው እንዳይሰጡ፣ እንዳይሸጡ እንዲሁም ስርቆትና ማጭበርበር እንዳይኖር፣ የወረዳው አስተዳደርም ሆነ የቀበሌ አስተዳደሮች እንዲሁም የግብርና ባለሙያዎች ጥብቅ ክትትል እንዲያደርጉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሰራው እንዲሳካ አስተዋፅኦ ላደረጉ ባለድርሻ አካላት የኮቾሬ ወረዳ አስተዳደር፣ ለሁሉም ቀበሌ አስተዳደርና ግብርና ባለሙያዎች፣ ለማሕበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬትና ከስሩ ለሚገኙ አስተባባሪ መመህራን እንዲሁም በቀንና በለሊት ለሚለፉ የችግኝ ጣቢያው ሰራተኞች ዶ/ር ደረጄ አመስግነዋል።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የ'ሆርቲካልቸር' ትምህርት ክፍል መምህርና የኮቾሬ ወረዳ ቡና ችግኝ ጣብያ አስተባባሪ አቶ ኢስማኤል ከሊል በበኩላቸው፤ በምርምር የለማ የቡና ችግኝ በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጥና በሽታ የመቋቋም አቅሙ ከፍ ያለ በመሆኑ ለአካባቢው ማሕበረሰብ ኑሮ መሻሻል የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
አያይዘውም አርሶ አደሮች የቡና ችግኙን የችግኝ ጣብያው ሰራተኞች ላለፉት ስምንት ወራት በከፍተኛ ጥረት እዚህ ደረጃ ማድረሳቸውን በመገንዘብ በአግባቡ አልምተው ለምርት እንዲያበቁ አሳስበዋል።
የኮቾሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽብሩ ምጁ በአንፃሩ፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ያለማቸውን የቡና ችግኞች በወረዳው ለሚገኙ አርሶ አደሮች በማሰራጨቱ ምስጋና አቅርበው፤ ለቡና ችግኝ ስርጭቱ በአጠቃላይ 176 ሞዴል አርሶ አደሮች ተመርጠው 63 ሺህ የቡና ችግኝ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
አክለውም፤ ዩኒቨርሲቲው በሰጠው ማሳሰቢያ መሰረት ችግኝ የወሰደ እያንዳንዱ አርሶ አደር በትክክል መትከሉን በመከታተል የሚፈጠር ክፍተት ካለም የእርምት እንደሚወስድ አቶ ሽብሩ ገልፀዋል።
የቡና ችግኝ ሲወስዱ ያገኘናቸው አርሶ አደር አቶ ኃይለማርያም ጠቀቦ እና ወ/ሮ ሃይማኖት ጎበና በሰጡን አስተያየት፤ በማሳቸው የነበረው የቡና ተክል በእርጅና ምክንያት የሚሰጠውን ምርት መቀነሱን አውስተው፤ በሽታ የሚቋቋምና በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጥ የቡና ችግኝ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ በመውሰዳቸው የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደሚያስገኝላቸው ገልጸውልናል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ