ለዲላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቀቀ

ዲ.ዩ፦ ህዳር 29/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማሕበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳሬክቶሬት ለዲላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞችና ባለሙያዎች ለሦስት ቀናት በህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ዙርያ ሲሰጥ የቆየውን ስልጠና አጠናቋል።
አቶ ብሩህ ተስፋሁን የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማሕበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳሬክቶሬት የአጫጭር ስልጠናዎች አሰተባባሪ እንደገለጹት በህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ዙርያ ክፍተት በሚታይባቸው ቦታዎች ላይ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል።
ስልጠናውን የተከታተሉት አቶ ሽመልስ መንገሻ የዲላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ እና የዳኝነት ስራ ሂደት አስተባባሪ በበኩላቸው የፍርድ ቤቶች ስራ በዋናነት በበዳይ እና ተበዳይ መካከል የሚነሱ ቅሬታዎችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ብይን መስጠት ነው ብለዋል።
ስለሆነም ይህ ውሳኔ በአገልግሎት አሰጣጥ ወቅት በየትኛውም ወገን በኩል ቅሬታ እንዳያስከትልና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መተግበር እንዲቻል ከስልጠናው ግንዛቤ እንደወሰዱ ነግረውናል።
ሌላዋ የስልጠናው ተካፋይ የነበሩት ወ/ሮ ሰናይት አለሙ የዲላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ በአንፃሩ በእውቀት ማነስም ይሁን በተለያየ ምክንያት የአገልግሎት አሰጣጡ እንዳይዛባና የተሻለ አተገባበር እንዲኖረው ለማድረግ ከስልጠናው ጠቃሚ እውቀት አግኝቻለሁ ብለዋል።
በስልጠናው ማጠናቀቂያ ንግግር ያደረጉት አቶ ታርኩ አለሙ የዲላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ባለፉት ጊዜያት በቅጥር ሂደትም ሆነ ሙያዊ ምክሮችን በማግኘት ረገድ ከዲላ ዩኒቨርስቲ ጋር ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል።
እንዲሁም በማሕበረሰቡ ውስጥ በተለያዩ ችግሮች ጠበቃ ማቆም ለማይችሉት ጥብቅና ከመቆም ጀምሮ የማማከር አገልግሎት ዩኒቨርሲቲው በነፃ እየሰጠ እንደሚገኝ አንስተዋል።
አሁንም ለቀረበው የስልጠና ጥያቄ በወቅቱ ምላሽ በመስጠት ዩኒቨርሲቲው ላደረገው ቀና ትብብር በዲላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ስም አቶ ታሪኩ ምስጋና አቅርበዋል።