በዲላ ዩኒቨርሲቲ በፐብሊክና ዲጅታል ዲፕሎማሲ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሄደ።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በፐብሊክ ዲፕሎማሲ የሚኖራቸው ሚና የላቀ በመሆኑ ምሁራን ቴክኖሎጂዎችን ሁሉ በመጠቀም ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር እንደሚጠበቅባቸው ተገለፀ።

..............

ዲ.ዩ ታህሳስ 1 ቀን 2014 ዓ.ም(ህ.ግ) የሳይንስ ሳምንት አካል በሆነው በፓናል ውይይት ላይ የተገኙ እንግዶችንና ተሳታፊዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዲላ ዩኒቨርሲቲ አስ/ተማ/አገ/ምክትል ፕሬዝዳንትና የፕሬዝዳንቱ ተወካይ ዶ/ር ዳዊት ሀዬሶ ይህ ወቅት መንግስት ለመንግስት ከሚያደርገው ዲፕሎማሲ ባሻገር ወደ ህዝብ ዲፕሎማሲ የተሻጋገርንበት ጊዜ በመሆኑ የህዝብ ዲፕሎማሲ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ገልጸው ይሁን እንጂ የህዝብ ዲፕሎማሲ ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር በጥንቃቄና በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ለአፍራሽ ተልዕኮ ሊውል እንደሚችል መገንዘብ እንዳለብን ተናግረዋል።

ከዚህ ባሻገር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላቸው ቁርኝነት እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ በተሻለ ሁኔታ በአግባቡ ተጠብቆ እንዲሄድ ግን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚኖራቸው ድርሻ የላቀ መሆኑን ምሁራኑ በመገንዘብ ዲጅታል ዲፕሎማሲ ላይ ከፍተኛ ሚና መጫወት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ዶ/ር ዳዊት አክለውም የህዝብ ዲፕሎማሲ ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ ያሉትን ቴክኖሎጂዎችን ሁሉ በመጠቀም ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ዲፕሎማሲ በማሸጋገር በተለይ የከፍተኛ ትምህት ተቋማት የራሳቸውን አሻራ ማኖር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዳይሬክተር ዶ/ር ኤርምያስ የማነ ብርሃን በበኩላቸው ዲጅታል ዲፕሎማሲን ውጤታማ በማድረግ ሂደት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ተመራማሪዎች ዋንኛ ትኩረታቸው ሊያደርጉ እንደሚገባ በማሳሰብ ለዚህም በቅርቡ ከፍተኛ ቁርጠኝነትና መስዋህትነት ያስከፈለን የውክልና ጦርነት በሳይንስ፣ የፐብሊክና ዲጅታል ዲፕሎማሲን ጥብቅ ቁርኝት ያረጋገጠ ብቻም ሳይሆን እንደ ሀገር ያለብንን ክፍተት ያሳየና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሊያከናውኑ የሚገባቸውን መሪ ተዋናይነት ያመላከተ መልካም አጋጣሚ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከፓናል ውይይቱ ጽሑፍ አቅራቢዎች መካከል የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህርና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ የሆኑት ወ/ት ሕይወት ዮሐንስ በበኩላቸው ዲላ ዩኒቨርሲቲ ጥቂት የራሳቸውን ፍላጎትና ጥቅም ለማስጠበቅ የተነሱ ቡድኖች የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎችን መሳሪያ አድርጎ በመጠቀም አገራችን ኢትዮጵያን ከማትወጣበት ትልቅ ችግር ውስጥ ለመክተት ርብርብ እያደረጉ ባለበት ሰዓት ላይ ይህን ወቅታዊ ውይይት ማዘጋጀቱ የሚያስመስግነው ትልቅ ተግባር እንደሆነ ገልጸው ውይይቱ ሰፊ ሃሳቦች ተነስተው የተንሸራሸሩበትና በተለይ ምሁራኑ እኔ ለሀገሬ የትኛው ጋር ነው የተሰለፍኩት ብሎ ቆም ብሎ እንዲያስብ ያስቻለ እንደነበር ገልጸዋል።