የዲላ ዩኒቨርሲቲ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ።

ዲ.ዩ ህዳር 6 ቀን 2014 ዓ.ም (ህ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ለጀግናው መከላከያ ሠራዊት ያሰባሰበውን ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አስረከበ።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የተደረገውን ድጋፍ ባስረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም የሀገርን ህልውና ለማስከበር ግዳጅ ላይ መስዋህትነትን እየከፈለ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት 3 ሚሊየን ብር በመለገስ አጋርነቱን ማሳየቱን ገልጸው ዛሬ ደግሞ ከዩኒቨርሲቲው ካፒታል በጀት 2 ሚሊዮን ድጋፍ እና ከሰራተኞች የወር ደሞዝ የተሰበሰበን በድምሩ 30 ሚሊዮን ብር እና በአይነት 200 ፍራሽ እንዲሁም 100 ተደራራቢ የብረት አልጋ ድጋፍ ማደረጉን ተናግረዋል ።
ዶ/ር ችሮታው አክለውም እንደ ሀገር ተገደን የገባንበትን የትግል ጦርነት በአሸናፊነት ለመቋጨትም ሆነ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ይዞ ለማስቀጠል ማሸነፍ የግድ ስለሆነ ሁሉም የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት በማሳሰብ ዲላ ዩኒቨርሲቲም የሀገርን ህልውና ለማስከበር በአሸባሪው ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ከግብ እስኪደርስ ዩኒቨርሲቲው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጠል ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ በበኩላቸው ሀገራችን አስቸጋሪ ፈተና በገጠማት በዚህ ወቅት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በአካል ጭምር በመቅረብ የሀገርን ህልውናን ለማስከበር ላሳዩት ከፍተኛ ድጋፍ በኢትዮጵያ ህዝብ ስም እና በጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ስም ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
በቢሾፍቱ በተካሄደው የርክክብ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የማህበረሰቡ ጉዳይ በዋናነት ይመለከተኛል በማለት ይህን ኃላፊነታቸውን ለተወጡ ዩኒቨርስቲዎች በራሳቸውና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስም ምስጋና በማቅረብ በቀጣይም ሌሎችም ዩኒቨርስቲዎች በፊት ያደርጉት ከነበረው በበለጠ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የቢሾፍቱ የመከላከያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አዛዥ ብ/ጄነራል ተገኝ ለታ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲዎች የዕውቀት ምንጭ ከመሆናቸው በተጨማሪ ለማህበረሰቡ ምሳሌ በመሆን ላሳዩት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በጀግና ሰራዊት ስም ምስጋና አቅርበው በቀጣይም በሌሎችም ጭምር ድጋፉ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል ።