የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፌራል ሆስፒታል የአይን ህክምና ማዕከል ከኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በጌዴኦ ዞን ከ8 ወረዳዎች ለመጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ነፃ የአይን ህክምና በይርጋ ጨፌ ከተማ እየሰጠ ይገኛል፡፡

ዲ/ዩ ጥቅምት 8/2014ዓ.ም (ህ.ግ) ጤናዉ የተጠበቀ ዜጋ ለሀገር እድገትና ብልጽግና ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር እዮብ አያሌዉ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የአይን ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪም ዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፌራል ሆስፒታል እና ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ከዛሬ ቀን ጀምሮ ለተከታታይ 6 ቀናት በአይን ሞራ ምክንያት ማየት ለተሳናቸዉ ወገኖች የአይን ህክምና እየሰጠ እንደሚገኝ ገልፀው የአይን ሞራ የሚከሰተዉ በእድሜ ምክንያት በመሆኑ ህመም ያለበት ሰዉ በጊዜ ወደ ጤና ተቋም በመምጣት መታከም ከቻለ የመዳን እድሉ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ ዉብሸት መኩሪያ የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትየጵያ በጌዴኦ፣ ቡርጂ እና አማሮ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ በበኩላቸዉ ከስምንት የጌዴኦ ዞን ወረዳዎች የተዉጣጡ ሰዎች በይርጋ ጨፌ 1ኛ ደረጃ ሆስፒታል ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፌራል ሆስፒታል እና ከሐዋሳ ሪፌራል ሆስፒታል በመጡ የአይን ህክምና ባለሙያዎች የአይን ሞራ ግርዶሽ የማስወገድ ኦፕሬሽን ማድረግ መጀመራቸዉን ተናግረዉ ለቀጣይ 6 ቀናት ከ300 በላይ ሰዎች በነፃ እንደሚረዱ አስታዉቀዋል፡፡
ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር ለህክምናው የሚያስፈልጉ ወጭዎችን የሚሸፍን ሲሆን ህክምናዉ በይርጋ ጨፌ ከተማ እንዲሆን የተፈለገበት ምክንያት ለታካሚዎች የቦታ ቅርበት ታሳቢ በማድረግ መሆኑን አቶ ዉብሸት አመልክተዋል፡፡
ከህክምናዉ ተጠቃሚ መሃከል ወ/ሮ ጠጂቱ በራሶ እና አቶ ካርቻ ኦጌ ዛሬ የዲላ ዩኒቨርሲቲ እና ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የሚሰጠዉን የነፃ የአይን ህክምና ሰምተዉ እንደመጡ ተናግረዉ ለበርካታ ጊዜያት በአይን ህመም ሲሰቃዩ መቆየታቸዉን ገልጸዋል፡፡ ዛሬ የመጡ የህክምና ቡድኖች የሠጡን ተስፋ ትልቅ በመሆኑ ተራ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸዉን ተናግረዋል፡፡