የዲላ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብን ችግር በዘላቅነት ለመፍታት እየሰራ መሆኑ ተገለፀ፡፡

ዲ.ዩ. ጥቅምት 07/2014 ዓ.ም. (ህ.ግ.) ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተቋቋሙበት አከባቢ ያለውን የማህበረሰቡን ችግሮች በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት መፍታት አንዱ የስራቸው አካል መሆኑን የተናገሩት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ኘሬዝዳንት ተወካይ ዶክተር ደረጄ ክፍሌ በይርጋጨፌና ኮቾሬ ወረዳዎች የደረሰውን የጎርፍ አደጋ አጥኝ በመመደብ የችግሩን መጠን በዝርዝር ለዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ካውንስል በማቅረብና ችግሩን በዘላቅነት ለማስቀረት ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ዛሬ በኮቾሬ ተገኝተው ድጋፉን በሚያበረክቱበት ወቅት ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አሉ ዶክተር ደረጄ በሁለቱም ወረዳዎች የደረሰው አደጋ ግዜ የማይሰጥ መሆኑን የተረዳው የዩኒቨርሰትው አስተዳደር ካውንስል ለጉዳዩ የተመደቡ አጥኝዎች ባቀረቡት ሪፖርት በመንተራስ ለግዜያዊ ድጋፍ የሚሆን የ250,500 (ሁለት መቶ ሀምሳ ሺህ አምስት መቶ) ብር ለምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲውል መወሰኑን አውስተው ይህ ድጋፍ በይርጋጨፌ ለ30 አባወራና በኮቾሬ ወረዳ ደግሞ ለ20 አባወራዎች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ ክብሩ አለሙ የማህበረሰብ አገልግሎት አጋርነት ዳይሬክተር በበኩላቸው ይህንን አደጋ በዘላቅነት ለመፍታት በኮቾሬ ወረዳ ወንዙ መስመሩን እየጣሰ ወደ ማህበረሰብ ማሳና መኖሪያ ቤት የሚፈሰውን ከመሰረቱ በማጥናት ዘላቂ መፍትሄ ለማግኝትና በይርጋጨፌ ወረዳ በየዓመቱ የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ ከመሰረቱ ለማስቀረት የምቻልበት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከሰብዓዊ ድጋፍ አንጻር በጊዜያዊነት ህብረተሰቡን ከችግሩ ከመታደግ አኳያ የፉርኖ ዱቄት፣ ፍራሽ፣ ብርድ ልብሰ፣ ዘይት፣ አተር ክክ እና ጨው መታደሉን ገልፀዋል፡፡
የኮቾሬ ወረዳ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ ገናናው የዲላ ዪኒቨርሲቲ ለደረሰብን አደጋ ፈጥኖ በመድረስ ባሳየው የወገን አሌኝታነት መደሰታቸውን ገልፀው ከእርዳታው በዘለለ ይህ አደጋ የማህበረሰብን ኑሮና ህይወት እንዳያመሰቃቅል በምሁራን እየተደረገ ያለው ጥናት እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል፡፡
ድጋፉን ስቀበሉ ያገኝናቸው ወ/ሮ ትዕግስት ገደቾና አቶ መስፍን ሀይሌ በአሁኑ ሰዓት ከቤት ንብረታችን በመፈናቀላችን አንስተን ለልጆቻችን የምንሰጠው በሌለበት ወቅት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፈጥኖ መድረሱ አስደስቶናል ብለዋል፡፡