14ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዲላ ዩኒቨርሲቲ በድምቀት ተከበረ።

ዲ.ዩ ጥቅምት 1 ቀን 2014 ዓ.ም (ህ.ግ) 14ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን "በአዲስ ምዕራፍ በተሟላ ሉዓላዊነት ለሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ" በሚል መሪ ቃል በዲላ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ስነ ስርዓቶች ተከበረ።
በአገራችን አዲስ ካቢኔ ተዋቅሮ መንግስት በይፋ ስራ የጀመረበት ወር ላይ ይህን የሰንደቅ ዓላማ ቀን ማክበራችን ልዩ ያደርገዋል ያሉት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሎታው አየለ ይህ ክቡር የሆነ ሰንደቅ ዓላማ በግዑዝ ሲታይ ከጨርቅ የተሰራ ይሁን እንጂ ውስጠ ሚስጥሩ ግን የኢትዮጵያ ማንነት መገለጫ የሆነ ብዝዎች የተሰውለት እና ብዝዎች ውድ ዋጋ የከፈሉለት ምልክት ከመሆኑም በላይ ለብዙ የአፍሪካ አገራት ጭምር ብሔራዊ ባንዲራ ሆኖ በማገልገል ላይ ያለ ሰንደቅ ዓላማ እንደሆነ ተናግረዋል ።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ይህን ባንዲራ የሚከተሉ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ይህን ምልክት ያደረጉበት ምክንያት ኢትዮጵያ ለብዙ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ መውጣት ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት በአፍሪካ ምድር ነፃነቷን አስጠብቃ የተገኘች ብቸኛ ሀገር በመሆኗ እንደሆነ ገልጸው እኛም ይህን ከኢትዮጵያ አልፎ በሌሎች ሀገራት ጭምር ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ስናከብር ከባንዲራው በስተጀርባ የተከፈለልንን ውድ ዋጋ በማሰብ በተሰማራንበት መስክ ሁሉ ለሀገራችን መስዋዕትነት ለመክፈልና ሀገራችንን ወደ ከፍታ ለማውጣት ቃል በመግባት ጭምር መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
በዩኒቨርስቲው በፕሬዝዳንት አደባባይ በተካሄደው የሰንደቅ ዓላማ ስነ ስርዓት የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞች እና ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ዝግጅቱ በዩኒቨርሲቲው ባህል ማዕከል ጣዕመ ዜማዎች እና በፌዴራል ፖሊስ የሀገሪን ሉዓላዊነትና ክብር በሚያወድሱ ትርዕቶች ደምቋል፡፡
ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተሻሻለው በሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 863/2006ዓ.ም አንቀጽ 2 መሰረት በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ በመጀመሪያው ሳምንት ሰኞ በሁሉም የመንግስት ተቋማት እንዲከበር መደንገጉ ይታወሳል።
.......................
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ትኖራለች