ዲላ ዩኒቨርሲቲ "ነጩ ፖስታ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት" ሃገራዊ ዘመቻን ተቀላቀለ።

ዲ.ዩ መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም (ህ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ የ"ነጩ ፓስታ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት" ዘመቻ መቀላቀሉን መልዕክት በማስተላለፍ ንግግራቸውን የጀመሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሎታው አየለ ይህ ሃገራዊ ዘመቻ የአሜሪካ መንግስት ይልቁንም ፕሬዝዳንቱ ሀገራችን ላይ የሚያደርጉትን ፍታዊ ያልሆነ ጫና እንዲቀንሱና ከእኛ ላይም እጃቸውን እንዲያነሱ ለማድረግ ታስቦ የተጀመረ ሃገራዊ ዘመቻ መሆኑን ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ አክለውም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ከዚህ ቀደም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሰላም በማስከበር ግዳጅ ላይ መስዋህትነት እየከፈለ ለሚገኘው የሀገር መከላኪያ ሠራዊት 30 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ድጋፍ በመለገሰ አጋርነቱን ማሳየቱን ገልጸው በቀጣይ ሳምንት ደግሞ ለተፈናቀሉ ወገኖች በአይነት ድጋፍ ለማድረግ እንደ ተቋም ዕቅድ መያዙን ገልፀዋል። የዲላ ዩኒቨርሲቲ አስ/ተማ/አገል/ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዳዊት ሀዬሶ በበኩላቸው የራሳችንን ሰላም እና ዕድገት የምንፈጥረው ራሳችን እንደመሆናችን መጠን የውስጥ አንድነታችንን ጠብቀን በአገራዊ አጀንዳዎች ላይ ያሉንን ክፍፍሎች በማስወገድ እና ትልቋን ኢትዮጵያን በመመልከት ይህን አስቸጋሪ ጊዜ በጋራ ቆመን በጋራ መሻገር እንዳለብን ተናግረዋል። የጌዴኦ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽ/ቤት ኃላፊና የዞኑ የዘመቻው አስተባባሪ ወጣት ደግነት ኃይሉ እንደተናገሩት የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ የሀገር ጉዳይ የእኛም ጉዳይ ነው በማለት ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ጀምሮ አጠቃላይ የዩኒቨርሲቲው ካውንስል በጋራ በመሆን አሻራቸውን ማሳረፋቸው የሚያስመሰግናቸው መሆኑን ገልጸው ፖስታው ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ በDHL በኩል በቀጥታ ወደ ዋይት ሀውስ እንደሚላክ ገልፀዋል:: በእለቱም የዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት በፕሬዚዳንቱና አስተባባሪዎቹ አስጀማሪነት መልዕክታቸውን ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት የፃፉ ሲሆን በቀጣይ ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የዘመቻው አካል እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል::