የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሪፌራል ሆስፒታል በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን የሲቲ ስካን (CT Scan) ማሽን አስገባ::

ዲዩ መስከረም 14/2014(ህ.ግ) አብዛኛውን ጊዜ የሪፌር ምክንያት ሆኖ የቆየውን ሲቲ ስካን ማሽን የህብረተሰብን ችግር በመረዳት መግዛቱን የተናገሩት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅና ሪፌራል ሆሰፒታል ም/ኘሬዝዳንት ዶ/ር ሰላማዊት አየለ በዚህ CT Scan ማሽን እጦት በርካታ የአከባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ መጉላላት ይደርስባቸው እንደነበር ገልፀው ማሽኑ የጌዴኦ ዞንን ጨምሮ እስከ ሞያሌ ድረስ ላሉ አጎራባች ማህበረሰብ ትልቅ አገልግሎት የሚሰጥና በዘርፉ ብቸኛ አገልግሎት ሰጪ ማሽን ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ይህ ማሽን በተለይም የትራፊክ አደጋ ለደረሰባቸዉ ታካሚዎች፣ ለካንሰር ሕክምና እና ለሌሎችም በሽታዎች ምርመራ የሚያገልግልና ለዘርፉም ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡
ታካሚዎች ለዚሁ አገልግሎት ወደ ሌላ ቦታ በመሄድ ለብዙ ዘመናት ለብዙ እንግልት ሲዳረጉ መቆየታቸዉን አውስተው በአጭር ግዜ ውስጥ የኢንስታሌሽን ስራው ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል ብለዋል፡፡
በዚሁ አጋጣሚ ይህ ማሽን እንዲገዛ እቅድ ከማቀድ ጀምሮ አስፈላጊውን ሁሉ እንዲሟላ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የኮሌጁና የዩኒቨርሲቲያችን የማኔጅመንት አባላትና ኃላፊዎች ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበው በቀጣይም ለህብረተሰቡ የሚያስፈልጉ የህክምና ቁሳቁሶችን ለማሟላት ዩኒቨርሲቲው በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ዶ/ር ሠላማዊት ተናግረዋል::