ዲላ ዩኒቨርሲቲ በክረምት የበጎ-ፈቃድ ሥራ የአቅመ ደካሞችን ቤቶች ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር አከናወነ፡፡

ዲ.ዩ. ጳጉሜ 04 ቀን 2013 ዓ.ም (ሕ.ግ) የአዲስ ዓመት መልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት በማስተላለፍ ንግግራቸውን የጀመሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ የበጎ ፈቃድ ሥራው በያዝነው ክረምት ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ገንዘብ በመመደብ በወናጎ ወረዳ 7 ቤቶች እንዲሁም በዲላ ከተማ 6 ቤቶች በድምሩ 13 ቤቶችን በ15 ቀናት ውስጥ ለተቸገሩ ቤተሰቦች ገንብቶ በማስረከብ በኢኮኖሚ አቅማቸው የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ ታስቦ የተጀመረ ፕሮግራም መሆኑን ገልጸዋል፡፡  ለመርሃ ግብሩ መሳካት ድጋፍ ያደረጉትንና በዕለቱም ተገኝተው ሥራውን በጋራ ያስጀመሩትን የዲላ ከተማ እና የወናጎ ወረዳ አስተዳደር ካቢኔ አባላትን አመስግነው ቤት ለሚታደስላቸው ቤተሰቦችም እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ ዶ/ር ችሮታው አያይዘውም እንዲህ ዓይነት ተግባር በቀጣይ አመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምር/ቴክ/ሽግ/ምክ/ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ በበኩላቸው የዲላ ከተማ አስተዳደር እና የወናጎ ወረዳ አስተዳዳር አቅም የሌላቸውን ቤተሰቦች በጥናት ለይተው ቤት እንዲታደስላቸው ማቅረባቸውን አመስግነው ዲላ ዩኒቨርሲቲ በአከባቢው የሚገኙ የማህበረሰብ ችግሮችን በጥናት በመለየት በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡  የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዘማች ክፍሌ በበኩላቸው ዲላ ዩኒቨርሲቲ በአከባቢው የሚገኝ ተቋም እንደመሆኑ መጠን የወሰደውን ተግባራዊ የልማት አጋርነት አድንቀው በቀጣይም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎችን በጋራ ወጥነን የሚንሰራባቸው መንገዶች ላይ በትኩረት እንንቀሳቀሳለን ብለዋል፡፡   የወናጎ ወረዳ ም/አስተዳደር እና አቃቤ ህግ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ሮቤ በበኩላቸው ዲላ ዩኒቨርሲቲ እንደማህበረሰብ አገልግሎት አስቦ ለተቸገሩ ቤተሰቦች በራሱ ተነሳሽነት የቤት እድሳት መሥራቱ እንዳስደሰታቸው ገልጸው በቀጣይም ችግር ያለባቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች በጥናት እየተለየ የበጎ ፈቃድ ሥራው በተለያዩ መንገዶች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸው ለሚያስፈልግ ትብብር ሁሉ የወረዳ አስተዳደሩ አብሮ እንደሚቆም ቃል ገብተዋል፡፡ ያነጋገርናቸው ቤት የሚታደስላቸው ቤተሰቦች ወ/ሮ ትዕግሰት መንግስቱ፣ ወ/ሮ አይናለም በለጠ እና ወ/ሮ ረሂማ ሳቢር ቤት ለማሳደስ አቅም እንደሌላቸው እና በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደነበሩ ገልጸው ስለተደረገላቸው ድጋፍ ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡