የዲላ ዩኒቨርሲቲ ለ2ኛ ዙር በቡና ልማትና ምርት ዝግጅት ያሰለጠናቸውን የግብርና ባለሙያዎች አስመረቀ

ዲ.ዩ. ነሐሴ 22 ቀን 2013 ዓ.ም (ሕ.ግ.) የዲላ ዩኒቨርሲቲ የቡና ምርምር ማዕከል ከጂ.አይ.ዜድ. ኢትዮጵያ አቅም ግምባታ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ከኢሉባቦር ዞንና ወረዳዎች ለመጡ 38 የግብርና ባለሙያዎች በቡና ልማት ምርት ዝግጅት፣ ጥራት ቁጥጥር እና ኤክስተንሽን ላይ የሰለጠኑትን ባለሙያዎች አስመረቀ፡፡ 

የዩኒቨርሲቲው አስ/ተማ/አገ/ም/ፕሬዚዳንት እና የፕሬዚዳንቱ ተወካይ ዶ/ር ዳዊት ሀዬሶ በመክፈቻ ንግግራቸው ዲላ ዩኒቨርሲቲ የቡና ጥራት ለማሻሻልና አለም አቀፍ የጥራት መስፈርት በሚጠይቀው ደረጃ ቡና ለማዘጋጀት እንዲቻል የቡና ምርምር ማዕከል በማቋቋም የተለያየ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸው ሠልጣኞች በሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀትና ልምድ ተጠቅመው ለሀገራችን ባለውለታ የሆነውን ቡና እንዲደግፉ፣ እንዲያሳድጉ እና ተገቢውን ቦታ እንዲይዝ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

ቡናችን በአለም አቀፍ ደረጃ ተገቢውን ቦታ እንዲያገኝ እና የአርሶ አደሩ ገቢ እንድያድግ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ የሚጠይቅ መሆኑን ዶ/ር ዳዊት አክለው ገልጸዋል፡፡ 

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምር/ቴክ/ሽግ/ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ በበኩላቸው ዲላ ዩኒቨርሲቲ ተወዳጅ የቡና ጣዕም ካላቸው የጌዴኦ-ይርጋ ጫፌና ኮቾሬ፣ ሲዳማ፣ አማሮ እንዲሁም በጉጂ በሚያዋስኑ አከባቢ የሚገኝ በመሆኑ ለቡና ልማት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ገልፀው የተሻሻለ የቡና ምርት በማረጋገጥ ብራንድ አድርጎ ለማውጣት በሳይንሳዊ መንገድ የገበሬውን ሥራ ለማገዝ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ሻፊ ኡመር የቡናና ሻይ ባለስልጣን ም/ዋ/ዳይሬክተር በበኩላቸው ዲላ ዩኒቨርሲቲ እንደ ሌሎች ዪኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን አሠልጥኖ ከማውጣት ባሻገር በቡና ላይ የዕውቀት ሽግግር በማድረግ ሠልጣኞች በንድፈ ሃሳብም በተግባርም ዕውቀት ቀስመው እንድወጡ በመሥራት ለኢኮኖሚ እድገት እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ 

ሥልጠናው በቡና ልማት ከችግኝ ዝግጅትና ተከላ ጀምሮ በማሳ እንክብካቤና በምርት ዝግጅት ጥራትና ቁጥጥር እንዲሁም በኤክስተንሽን ላይ ያተኮረ እንደነበረ የገለፁት የዲላ ዩኒቨርሲቲ የቡና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር አለሙ ዴሳ የሥልጠናው ዋና አላማ የአርሶ አደሩ ማሳ እሴት እንዲጨምር÷ የአመራረት ዘይቤውን ዘመናዊ እንዲያደርግ እና የተሻለና ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለገበያ አቅርበው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንድሆኑ ለማስቻል ነው ብለዋል፡፡

የGIZ ተወካይ አቶ ታዬ አባተ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ለተመራቂዎች አስተላልፈው ሠልጣኖች ወደመጡበት ስመለሱ ከስልጠናው ባገኙት ዕውቀትና ልምድ አርሶ አደሩን እንዲደግፉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ 

ያነጋገርናቸው በስልጠናው ቆይታቸው ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተመራቂዎች ጌትነት ሽፈራው እና ይመኙሻል ዘገየ እንደተናገሩት የንድፈ ሃሳብ ትምህርት በክፍል ከመውሰዳቸው ባሻገር የተግባር ሥራ በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ በመሥራት በቂ ዕውቀት እንዳገኙ ገልጸው በቀጣይ በሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀትና ልምድ በቴክኖሎጂ በመታገዝ እስከታች በመውረድ አርሶ አደሩን እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡

እንኳን ደስ አላችሁ! እንኳን ደስ አለን! ..... ትኩስና ወቅታዊ መረጃ እንዲደርስዎ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሚዲያዎችን ይጎብኙ፣