በዲላ ዩኒቨርሲቲ የዜሮ ፕላን ተሞክሮ የልምድ ልውውጥ እና ምክክር መድረክ ተካሄደ

ዲዩ ፡ 13/12/ 2013 ዓ.ም (ሕ.ግ) በዲላ ዩኒቨርሲቲ ኤች.አይ.ቪ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት እና የሴቶች÷ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለተማሪዎች ምቹ ስፍራ የዜሮ ፕላን በሚል የልምድ ልውውጥ እና ምክክር መድረክ አካሄደ፡፡
በመክፈቻ ንግግራቸው ወደ ዩኒቨርስቲው የመጡ እንግዶችና ተሳታፊዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ ያሉት የዲላ ዩኒቨርሲቲ የአስ/ተማ/አገልግሎት ም/ኘሬዚዳንት እና የፕሬዚዳንቱ ተወካይ ዶ/ር ዲዊት ሀዬሶ ዜሮ ፕላን የተማሪዎች አደረጃጀት በዋናነት የተዋቀረው በሥነ-ተዋልዶ ዙሪያ ግንዛቤን ለመፍጠር፣ በዚህ ምክንያት የሚመጡ የሥነ-ልቦና ጫናዎችን ለመቀነስ፣ እርስ በእርስ በትምህርትና በማህበራዊ ሕይወት እንዲረዳዱ ለማድረግና አብሮነትን ለማጠናከር እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ እና በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሴቶች÷ ወጣቶች እና ህጻናት ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ማህሌት በቀለ ለፕሮግራሙ አዘጋጆች ምስጋናቸውን አቅርበው የዩኒቨርሲቲውን መልካም ተሞክሮ እና ልምድ ለሌሎችም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተደራሽ ለማድረግ ክትትልና ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል፡፡
የዲላ ዩኒቨርሲቲ የሴቶች ወጣቶች እና ህጻናት ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ አለም ብርሃኑ በበኩላቸው ዳይሬክቶሬቱ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አስተዋውቀው የአገራችን ሴቶች በባህል ተፅዕኖ ስር የነበሩ ሲሆን ከዚህም ተፅዕኖ አልፈው ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የገቡትን ሴቶች ከፆታ አቻዎቻችው ጋር በመሆን ለውጤት ማብቃት የሁሉም ድርሻ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሀገር አቀፍ የሆነ የውይይትና የልምድ ልውውጥ መድረክ መዘጋጀቱን የተናገሩት የዲላ ዩኒቨርሲቲ HIV መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ሸፈራው የዚህ ዝግጅት አስተባባሪ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒሰቴር ሲሆን ከ46ቱም ዩኒቨርሲቲዎች የጀንደር ዳይሬክቶሬቶች÷ የሴት ተማሪ አሰተባባሪዎች እና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒሰቴር ተወካይ ዳይሬክተሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውን ተናግረዋል::
የዝግጅቱ ዋናው ዓላማም በዲላ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረውንና ለመማር ማስተማሩ ሥራ ትልቅ እገዛ እያደረገ ያለውን የዜሮ ኘላን ወደየ ተቋማቱ ማስፋት መሆኑንም ገልፀዋል::
በተጨማሪም የኢት/ያ ከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ህብረት አመራር ም/ኘሬዚዳንት አብረሀለይ አረፋይሌ፣ የሀገር አቀፍ ከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ህብረት ተቋማት የሴቶች ጉዳይ ዘርፍ ተጠሪ ሜሮን ዓለሙ፣ እንዲሁም የ DKT Ethiopia የስነ-ተዋልዶ ጤና ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሽመልስ ገበየሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡