የዲላ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ለተመራቂ ተማሪዎች “ህይወት ከምረቃ በኋላ” በሚል ርዕስ ስልጠና ሰጠ፡፡

ዲ.ዩ ሐምሌ 27/2013 ዓ.ም (ህ.ግ) የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎች ልዩ የሚያደርጋቸው በኮቪድ 19 ምክንያት ትምህርት ተቋርጦ ስለነበረ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ሲመለሱ በጊዜ እጥረት ከባድ ጫና የነበረባቸው ሲሆን ይህን ተግዳሮት ተቋቁመው ለዚህ ቀን መድረሳቸው በጣም አስደሳች መሆኑን የተናገሩት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተወካይና አስ/ተ/አ/ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዳዊት ሀዬሶ ተማሪዎች ተመርቀው ወደ ስራ ዓለም ሲቀላቀሉ በስነ-ምግባር ታንጸው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት እና ራሳቸውን ከብልሹ አሰራር እና ሙስና በመጠበቅ ወገናቸውን እና ሀገራቸውን ወደተሻለ የእድገት ደረጃ ለማድረስ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የዲላ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ መብራቴ ሽፈራው ለተመራቂ ተማሪዎች ባሰሙት ንግግር ተማሪዎች የቀሰሙትን ዕውቀትና ክህሎት ለግል ጥቅምና ርካሽ ተግባር መፈፀሚያ እንዳይውል በማድረግና በመልካም ስነ-ምግባር ማህበረሰባቸውን እንዲያገለግሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ወ/ሮ መብራቴ አክለውም በዕድገታችን ላይ እንቅፋት የሆነውን ሙስናና ብልሹ አሰራር በመጠየፍና ተፈፅሞ ሲገኝ በማጋለጥ በአቋራጭ ለመክበር የሚደረገውን ሩጫ ለመግታት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ አደራ ሰጥተዋል፡፡
ከሠልጣኞች ያነጋገርናቸው ተመራቂ ተማሪ ሙሴ እና ተማሪ ሰይድ በበኩላቸው ያገኘነው ስልጠና በሙያችን ለሕብረተሰባችን በመልካም ስነ-ምግባር እና በጥሩ ስብዕና እንድናገለግል በነበረን ዕውቀት ተጨማሪ ግንዛቤ አስጨብጦናል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ህዝብና ሀገርን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ወደ ስራ ዓለም የምንገባበት ምዕራፍ ላይ ባለንበት ጊዜ ስልጠናው ስለተሰጠን ለቀጣይ ህይወታችን ጥሩ ስንቅ ይሆናል ብለዋል፡፡