ተመራቂ ተማሪዎችን ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር የሚያገናኝ የሥራ አውደ ርዕይ ተካሄደ

ዲዩ፤ ሰኔ 14 ቀን 2011 ዓ.ም (ህዝብ ግንኙነት) በዲላ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎችን ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር የሚያገናኝ የሥራ አውደ ርዕይ ተካሄደ ፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየዓመቱ በርካታ ተማሪዎችን ያስመርቃሉ፡፡ ከሚመረቁት ተማሪዎች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ሥራ እንደሚያገኙ ትምህርት ሚኒስቴር ከሁለት ዓመት በፊት ባስጠናው ጥናት ተመላክቷል፡፡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ፣ የሥራ ፈጠራና የመምራት ክህሎት ማነስ እንዲሁም የሙያ ስነ-ምግባር ችግሮች ተመራቂዎች በቀጣሪ ድርጅቶች ተመራጭ እንዳይሆኑ የሚያደርጉ ምክንያቶች መሆናቸውን ጥናቱ አመላክቷል፡፡ ችግሮችን ለመፍታትና የተመራቂዎችን የመቀጠር ዕድል ከ60 ወደ 80 በመቶ ከፍ ለማድረግ ሰባት ስትራቴጅዎች ተቀርፀው ሥራውን በበላይነት የሚያስተባብሩ የሥነ-ውጤት (Deliverology) ጽ/ቤቶች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲቋቋሙ ተደርጓል፡፡ ከስትራቴጅዎች መካከል ተመራቂዎችን ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ማገናኘት (JOB FAIR) አንዱ በመሆኑ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ስነ-ውጤት ዳይሬክቶሬት ከኢንዱስትሪ ግንኙነትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ጋር በመቀናጀት የዘንድሮ ተመራቂዎችን ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ያገናኘ የምክክርና የሥራ አውደ ርዕይ መድረክ በዩኒቨርሲቲው መሠብሰቢያ አዳራሽ አካሂዷል፡፡ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ብቁ ዜጎችን በማፍራት ለሀገር ሲያበረክት መቆየቱን ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር ችሮታው አየለ በፕሮግራሙ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር ጠቁመዋል፡፡ ተመራቂዎች ወደ ሥራ ዐለም ሲሰማሩ በስነ-ምግባራቸው ምስጉን፣ ምርታማና አርአያ ሊሆኑ እንደሚገባ ያሳሰቡት ፕሬዚዳንቱ ቀጣሪ ድርጅቶችም አዳድስ ምሩቃንን ቢቀጥሩ ስኬታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ ተመራቂዎች በቀጣሪ ድርጅቶች ተመራጭ እንዲሆኑ ከመደበኛ ትምህርት ጎን ለጎን ጥናትን መሠረት ያደረገ የስነ-ምግባር፣ እንግሊዝኛ ቋንቋ፣ ፈጠራና መሪነት ላይ የክህሎት ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን የዩኒቨርሲቲው ስነ-ውጤት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መምህር ሞቲ ሞሲሳ ተናግረዋል፡፡ የተመራቂዎችን የመቀጠር ምጣኔ ከፍ ለማድረግ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮ ተመራቂዎችን ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ለማገናኘት በተዘጋጀው ፕሮግራም የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የግንባታና ህዋዌ ድርጅቶችን ጨምሮ ሃያ የሚሆኑት መገኘታቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር የሚችሉ ምሩቃን ቁጥር እያደገ መምጣቱን የገለፁት ደግሞ የኢንዱስትሪ ግንኙነትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ዳይሬክተር ዶ/ር ደሳለኝ ጴጥሮስ ናቸው፡፡ ከትልልቅ ድርጅቶች ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግና ግብዓት በማቅረብ ተማሪዎች ለሀገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጉልህ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ የፈጠራ ውጤቶችን መሥራት ችለዋል ብለዋል፡፡ የምህንድስና የትምህርት መስኮች ተመራቂ ተማሪዎች የሠሩትን የፈጠራ ውጤት አቅርበዋል፡፡ የተገኙት የድርጅት ተወካዮችም ሊቀጥሯቸው እንደሚፈልጉ ገልፀዋል፡፡