በዲላ ዩኒቨርሲቲ በአረንጓዴ አሻራ ቀን

በዲላ ዩኒቨርሲቲ በአረንጓዴ አሻራ ቀን ከ10 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞች ተተከሉ ዲዩ፤ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም (ህዝብ ግንኙነት) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ የአረንጓዴ ቀንን ምክንያት በማድረግ በተቋሙ የዕፅዋት ጥበቃና ኢኮ-ቱሪዝም ማዕከል ችግኝ ተከለዋል፡፡ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በታሪካዊው ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ቀን የተቋሙ አመራሮች፣ ሠራተኞችና ተማሪዎች በነቂስ ወጥተው በችግኝ ተከላው ተሳትፈዋል፡፡ በተያዘው ዓመት ለአካባቢ ጥበቃ ልዩ ትኩረት በመስጠት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው ጥሪ ሁሉንም ያነቃና አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ ተናግረዋል፡፡ የበረሀማነት መስፋፋትን ለመግታትና ብዝሀ ህይወትን ለመጠበቅ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት መሠጠቱ አስፈላጊ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ማኅበረሰቡ ችግኝ ከመትከል ባለፈ የመንከባከብ ባህል ማዳበር ይኖርበታል በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ለመማር ማስተማር፣ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ሀገር በቀል ችግኞች መተከላቸውን የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬህይወት እንዳለ ተናግረዋል፡፡ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ለአካባቢ ጥበቃ በሰጠው ትኩረት የእጽዋት ጥበቃና ኢኮ ቱሪዝም ማዕከል አቋቁሞ ሰፊ የሆነ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡