በአቀባበል ስነ – ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ከበደ ግዛው፣ በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያ፤ ትምህርት ሚኒስቴር እንደ ሀገር የመጡ የሪፎርም ለውጦችን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከማጠናከር አንፃር በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እየተገበረ ባለው አቅጣጫ መሠረት አሁን ላይ የትምህርት ተቋማት አለም አቀፋዊነት ይዘት እንዲኖራቸው ትልቅ ስራ እየሰራ እንደሆነ በመግለጽ፤ ዶ/ር ኤልያስ ወደ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በፕሬዝዳንትነት እንዲመጡ መደረጉን ገልጸዋል።
አቶ ከበደ ግዛው አያይዘውም፤ አዲሱ ፕሬዝዳንት በተቋሙ የአመራር ማዕከላዊነትን ማስጠበቅ እንደሚኖርባቸው በማስገንዘብ በቀጣይ ዩኒቨርሲቲው ብቃትን እና ችሎታን ብቻ መሠረት ያደረገ የመዋቅር ምደባ እንዲያካሂድ መልዕክታቸውን በማስተላለፍ አዲስ ለተመደቡት ፕሬዚዳንት መልካም የስራ ዘመን ተመኝተዋል።
ተመሳሳይ የፕሬዝዳንቶች ምደባ በሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ፤ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ያስቀመጠውን የሪፎርም ስራ መሬት አውርዶ ውጤታማ ለማድረግ የዚህ ካውንስል ሚና የላቀ በመሆኑ ስራዎችን ለማሳካት ጥረት እንደሚያስፈልግ አቶ ከበደ አያይዘው ተናግረዋል።
በመድረኩ የቀድሞ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር)፣ በተቋሙ ላለፉት ስድስት አመታት ለነበራቸው የአገልግሎት ቆይታ ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልልና ለጌዴኦ ዞን አመራሮች፣ ለዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ ለዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ለካውንስል አባላት እና ሠራተኞች ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፤ በዩኒቨርሲቲው አዲስ ለተመደቡት ፕሬዝዳንት እንኳን ወደዚህ ተቋም በሰላም መጡ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዶ/ር ችሮታው አያይዘውም፤ በተቋሙ በዚህ ሁኔታ የስልጣን ርክክብ መደረጉ ትልቅ እድል መሆኑን በመጥቀስ፤ ለዚህም በተቋሙ የተረጋጋ ሁኔታ መፍጠር የተቻለው ህግና ስርዓትን በማስጠበቅ በዩኒቨርሲቲው ፍጹም ሰላማዊ ተቋም በመፈጠሩ እንደሆነ አስታውሰው አዲሱ ፕሬዝዳንትም ይህንን አስጠብቆ እንደሚቅጠል እምነታቸው እንደሆነ በመግለጽ ለዶ/ር ኤልያስ መልካም የስራ ዘመን እንዲሆንላቸው ዶ/ር ችሮታው አየለ ተመኝተዋል።
አቀባበል የተደረገላቸው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኤልያስ አለሙ በበኩላቸው፤ እንደ አንድ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ተማሪ በዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንትና ካውንስል አባላት ይህን የመሰለ ትልቅ አቀባበል ተደረጎ ዳግም በዚህ ሁኔታ በዩኒቨርሲቲው በመገኘታቸው ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረላቸው ገልጸው፤ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዶ/ር ኤልያስ አክለውም፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲው በርካታ ምሁራንን ያፈራ ተቋም እንደመሆኑ መጠን ይህንን የተማርኩበትን ዩኒቨርሲቲ በዚህ የታሪክ አጋጣሚ በፕሬዝዳንትነት እንድመራ በትምህርት ሚኒስቴር ስለተመደብኩ የተሰማኝ ስሜት ከፍተኛ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም፤ በቀጣይ ዋና ስራቸው የሚሆነው ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር በመሆን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ያስጀመሯቸውን ጠንካራ ጎኖች ከነጥንካሪያቸው ማስቀጠልና እንዲሁም ውስንነት የነበረባቸው ጉዳዮችም ካሉ እያስተካከሉ መሄድ መሆኑን በመግለጽ፤ ለዚህም የዩኒቨርሲቲውን ተልዕኮ ለማሳካት በጋራ ሁሉም ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅበት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከአቀባበል መርሃ – ግብሩ በኃላ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት አባላት በተገኙበት አዲሱ ፕሬዝዳንት ከቀድሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ችሮታው አየለ ጋር ቀጣይ በሚተገበሩ ዋና ዋና ስትራቴጂያዊ የስራ ጉዳዮች ላይ ገላጻ ተደርጎላቸው የስራ ርክክብ እና የመስክ ምልከታ አካሄደዋል።
ዶ/ር ኤልያስ አለሙ፤ ከዚህ ቀደም በጂንካ ዩኒቨርሲቲ በምክትል ፕሬዝዳንትነት ቦታ ሲያገለግሉ የቆዩ መሆናቸው በመድረኩ ተገልጿል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲም ለዶ/ር ኤልያስ አለሙ መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው መልካም ምኞቱን ይገልጻል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
FB: https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram:https://t.me/dprd9
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et







