ዲ.ዩ፤ ሚያዚያ 11/2016 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት በጌዴኦ ዞን ቡሌ ወረዳ ለሚገኙ ሞዴል አርሶ አደሮች በምርምር የለማ የምርጥ ዘር ድንች ስርጭት አካሂዷል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተካልኝ ታደሰ፤ ዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ ከመማር ማስተማር እና ከምርምር ስራዎች ባለፈ በርከት ያሉ የማህበረሰብ ተደራሽ ፕሮጀክቶችን በመስራት ለአካባቢው ህብረተሰብ ተጠቃሚነት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ከእነዚህም መካከል በዛሬው ዕለት በቡሌ ወረዳ ለሚገኙ ከአምስት ቀበሌ ለተመረጡ 80 አርሶ አደሮች የምርጥ ዘር ድንች መስራጨቱን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ተካልኝ ገለፃ፤ አካባቢው በብዛት የድንች ምርት ያለበት አካባቢ እንደመሆኑ አርሶ አደሩ እስካዛሬ ዘር ሲፈልግ ከሌላ አካባቢ ያመጣ እንደነበርና አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ማዕከሉን በአካባቢው አቋቁሞ ዘርን በማዘጋጀት ማሰራጨቱ ህብረተሰቡን ከብዙ እንግልትና ወጪ ማዳን ማስቻሉን ተናግረዋል።
በቀጣይም ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በመሆን እዚሁ የድንች ቴክኖሎጂ ሽግግርና ስልጠና ጣቢያ ውስጥ እየሰሩ ያሉ ወደ 30 የሚጠጉ ሰራተኞችን የድንች ዘርን በራሳቸው አዘጋጅተው በመሸጥ በገቢ ራሳቸውን እንዲችሉና እንዲሁም አካባቢውንም የዘር ምንጭ እንዲሆን ለማስቻል አሁን ላይ ከወረዳው አስተዳዳር ጋር ስምምነት ላይ ተደርሶ ወደ ተግባር ለመግባት እየተሰራ መሆኑን አቶ ተካልኝ አያይዘው ተናግረዋል።
የቡሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በራቆ በራሶ በበኩላቸው፤ አካባቢው ደጋማ አካባቢ እንደመሆኑ መጠን ዩኒቨርሲቲው ይህን የምርጥ ዘር ድንች በምርምር በተደገፈ መልኩ አዘጋጅቶ ለአርሶ አደሩ ማሰራጨቱ በአካባቢው የድንች ምርት ጥራትን ከማሳደግ ባለፈ የህብረተሰቡንም የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የቡሌ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዘሪሁን አለሙ እንዲሁ፤ ድንች በወረዳው ላይ ህብረተሰቡ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከሚጠቀማቸው የሰብል ዝርያዎች ከፍተኛ ቦታ የሚይዝ እንደመሆኑ፤ ዩኒቨርሲቲው በአርሶ አደሩ አካባቢ ያለውን የዘር ችግር ተረድቶ በአካባቢው የምርምር ማዕከል በማቋቋም በምርምር የተለዩ የምርጥ ዘር ድንቾችን ለህብረተሰቡ ለሁለተኛ ጊዜ ማሰራጨቱ የሚያስመሰግነው ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የሆርቲካልቸር ትምህርት ክፍል መምህርና የቡሌ ወረዳ የምርጥ ዘር ጥናትና ምርምር አስተባባሪዎች የሆኑት መምህር ንጉሱ ደበበ እና መምህር ጨምር ጨዋቃ እንደገለጹት፤ ዛሬ በማዕከሉ በምርምር ተለይቶ ለስርጭት የበቃው ምርጥ ዘር ድንች “ጉዳሌ” የተሰኘው ዝርያ እንደሆነ ገልጸው በዚህም ለዘንድሮ ለስርጭት ከታሰበው አንድ መቶ ኩንታል ውስጥ ለ80 አርሶ አደሮች ለእያንዳንዳቸው አንድ አንድ ኩንታል በጥቅሉ 80 ኩንታል ምርጥ ዘር ድንች መሰራጨቱን አስረድተዋል።
ምርጥ ዘር ድንች ሲወስዱ ያገኘናቸው አቶ ገበየሁ ሾቶላ እንዲሁም ወ/ሮ የኔነሽ ወርቁ፤ የድንች ስርጭቱ ለቤተሰባቸው የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ በገቢም ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርግ በመሆኑ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
እነዚህ አርሶ አደሮች ከስርጭት ያገኙትን ምርጥ ዘር ከምርት በኃላ በቀጣይ እነሱም ለ80 አርሶ አደሮች በቅብብሎሽ የሚስተላልፉ መሆናቸውን ከአዘጋጆች ያገኘነው መረጃ ይገልጻል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ፤
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
Facebook:
https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://www.t.me
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et