ለአቅመ ደካማ የማህበረሰብ ክፍሎች ቤት የማደስ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ተካሄደ

ዲ.ዩ፦ የካቲት 14/2015 ዓም (ህ.ዓ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት አባላት በይርጋጨፌና ወናጎ ወረዳዎች ለሚገኙ አቅመ ደካሞች የቤት የማደስ በጎ ፍቃድ አገልግሎት አስጀመሩ።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዝዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ ባለፉት አመታት በዲላ እና ወናጎ አካባቢ የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስና የተወሰኑ ለቤት ቁሳቁስ የሚሆኑ እቃዎችን በልዩ ሁኔታ የመደገፍ ስራ ተሰርቶ ነበር ብለዋል። በዘንድሮው አመትም ይህንኑ መሰል በጎ ፍቃድ አገልግሎት በይርጋጨፌ እና ወናጎ ወረዳዎች ለማከናወን ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ፕሬዝዳንቱ አክለው ገልፀዋል።
ዩኒቨርሲቲው እየሰራ ያለው ስራ ለአከባቢው ባለሀብት እና አስተዳደር አነሳሽ በመሆኑ እንደዚህ አይነት የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመርዳት መትጋትና መቀናጀት እንደሚገባም ዶ/ር ችሮታው አሳስበዋል።
ደረጄ ክፍሌ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ኘሬዝዳንት በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን እየሰጠ መቆየቱን አንስተው፤ የአቅመ ደካሞችን ቤትና ህይወት በመቀየር የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ማድረግ አንዱ ተግባር ነው ብለዋል።
ዛሬ በይርጋጨፌ ከተማ የተጀመረውን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የከተማ አስተዳደሩ ለይቶ ያቀረባቸውን አቅመ ደካሞች ያረጁ ቤቶችን አፍርሶ በተሻለ የመስራት ስራ መጀመሩን ነው ዶ/ር ደረጄ የገለፀው።
ዶ/ር ደረጄ አያይዘውም ባለፈው የበጀት ዓመት በወናጎ ሰባት(7) እና በዲላ ስድስት (6) መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ማስረከባቸውን አስታውሰዋል። በአሁኑ ደግሞ በይርጋጨፌ አምስት (5) እና በወናጎ አምስት (5) በድምሩ አስር (10) ቤቶችን በሁለት ነጥብ ሶስት ሚሊየን ብር ሰርቶ ለማስረከብ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
ለዚህ ስራ መሳካትም አራት በጎ ፍቃደኛ መምህራን ከኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል መሳተፋቸውን ዶክተር ደረጄ አያይዘው ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክተር አቶ ተካልኝ ታደሰ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ከሚሰጣቸው ሙያዊ በጎ ፍቃድ አገልግሎቶች መካከል አንዱ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም መምህራንም በሙያቸው ከፍተኛ እገዛ ለማህበረሰቡ በመስጠት ላይ ናቸው ብለዋል።
በሌላ በኩል የይርጋጨፌ ከተማ ከንቲባ አቶ ታደለ ጥላሁን ዲላ ዩኒቨርሲቲ በከተማም ሆነ በዞን ደረጃ እየሰራ ባለው ዘርፈ ብዙ ስራ ከፍተኛ ቅቡልነትን እያገኘ መምጣቱን ጠቅሰዋል። አሁን ላይ የአቅመ ደካማ የማህበረሰብ ክፍሎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ያሳየው ቁርጠኝነት የሚያስመሰግንና ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ መልካም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የቤት እድሳት ከሚደረግላቸው ሰዎች መካከል ወ/ሮ በቀለች በራሶ፣ የዘጠኝ ቤተሰብ አስተዳዳሪ እና ወ/ሮ ዘነበች ታደሰ የአራት ቤተሰብ አስተዳዳሪ በአገልግሎቱ መደሰታቸውን ገልፀውልናል።
የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እናቶች ዝናብ በመጣ ቁጥር የነበረባቸው ሀሳብና ጭንቀት ከባድ እንደነበር አስታውሰው፥ ይህ ችግር ሊቀረፍላቸው በመሆኑ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸውልናል። ዲላ ዩኒቨርሲቲ በዚህ መልኩ አቅመ ደካሞችን የሚጠቅም ሀሳብ ይዞ ወደ ስራ በመግባቱ አመስግነዋል።
..................
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
ተክክለኛ እና ወቅታዊ ተቋማዊ መረጃ ለማገኘት
#ቴሌግራም፦ University of the Green Land
ይከታተሉን!
ለጥያቄና አስተያየተዎ
#ኢሜይል፦ pirdir@du.edu.et
ይላኩልን