በቤተ- ሙከራ አደረጃጀትና አጠቃቀም ዙርያ ስልጠና ተሰጠ

ዲ.ዩ፦ ሕዳር 29/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) በዲላ ዩኒቨርሲቲ ማሕበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሳይንስ መምህራን በቤተ ሙከራ አደረጃጀትና አጠቃቀም ዙሪያ ስልጠና ተሰጥቷል።
በዩኒቨርስቲው የማሕበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተካልኝ ታደሰ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ፍኖተ ካርታ መሰረት በሀገር አቅፍ ደረጃ 55 በመቶ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ እንዲሁም 45 በመቶ ደግሞ የማሕበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች እንዲሆን አቅጣጫ መቀመጡን አስታውሰዋል።
ይሁን እንጅ ባለፈው የትምህርት ዘመን በተደረገው የዳሰሳ ጥናት በጌዴኦ ዞን ባሉት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 26 በመቶ ተፈጥሮ ሳይንስ እና 74 በመቶ የማሕበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች እንደሆነ ውጤቱ ያሳያል።
በዚህ ሂደት የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ለማግኘት አስቸጋሪ እንዳይሆን ከወዲሁ መፍትሔ ለመፈለግና ዲላ ዩኒቨርሲቲ የበኩሉን ሚና ለመወጣት ስልጠና ማዘጋጀቱ ተገልጿል።
በቀጣይም ከዞኑ ትምህርት መመሪያ እና ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን መምሪያ ጋር በቅርበትና በቅንጅት እንሰራለን ነው ያሉት አቶ ተካልኝ በስልጠናው።
ከአሰልጣኞች መካከል መምህር በፍቃድ ተድላ በበኩላቸው ስልጠናው ለሳይንስ መምህራን በቤተ ሙከራ አደረጃጀትና አጠቃቀም ላይ ማዕከል ያደረገ ሆኖ ለኬሚስትሪ እና ፊዚክስ ትምህርቶች ትኩረት የሰጠ ተግባር ተኮር ስልጠና ነው ብለዋል።
ሰልጣኞች በቀላሉ በአካባቢው የሚገኙ ግብአቶችን ተጠቅመው እንዴት ቤተ-ሙከራ ማደራጀት እንደሚችሉ፣ በተደራጀ ቤተ-ሙከራ በአከባቢው በሚገኙ እጽዋትና አበቦች ተጠቅመው ተማሪዎቻቸውን ተግባር ተኮር ትምህርት ማስተማር እንዲችሉ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ታስቦ ነው ስልጠናው የተዘጋጀው።
በጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ መምህራንና ትምህርት ልማት ቡድን መሪ አቶ ንፁ ከበደ በበኩላቸው የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት በተማሪዎች ተፈላጊ እንዲሆን በተግባር የተደገፈና ሳቢ የመማር ማስተማር ዘዴ የሚከተል ማድረግ እንዲሆን ይሰራል ብለዋል።
ይህን እውን ለማድረግም ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተሻለ የቤተ-ሙከራ እውቀትና ክህሎት ያላቸው መምህራንና የቤተ-ሙከራ ባለሙያዎች በጌዴኦ ዞን በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መመረጣቸውን አመላክተዋል።
ስልጠናውን አጠናክሮ በመቀጠል የተፈለገውን ውጤት ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግም አቶ ንፁ አክለው ገልጸዋል።
ስልጠናው በጌዴኦ ዞን ከሚገኙ ሃያ ስድስት (26) ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተወጣጡ ሃያ ስምንት (28) የተፈጥሮ ሳይንስ መምህራንና የቤተ-ሙከራ ባለሙያዎች ለሶስት ቀናት ተሰጥቷል።