ምርምር ስራዎች ዙሪያ ውይይት ተካሄደ

ዲ.ዩ፦ ሕዳር 19/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ጽ/ ቤት ከምርምርና ስርጸት ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር በምርምር ስራዎች ዙርያ ሁለተኛ ዙር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
ዶ/ር ችሮታው አየለ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት በአሜሪካ ኢምባሲ ጋባዥነት ዘጠኝ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች፣ አስራ አምስት ምክትል ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም ሁለት የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያዎች የተካተቱበት ጉብኝት በአሜሪካ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች አደርገው መመለሳቸው ይታወሳል።
ዶ/ር ችሮታው በአሜሪካ ቴክሳስ ቴክ፣ ኦክላሆማ ስቴት እና ኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲዎችን በጎበኙበት ወቅት ያገኙትን ልምድ ለጉባኤው ተሳታፊዎች አካፍለዋል።
ዶ/ር ችሮታው በመድረኩ እንደገለጹት የጎበኟቸው የትምህርት ተቋማት የሰሩትንና እየሰሩ ያሉትን ጠንካራ ስራዎች ከሀገራችንና ተቋማችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ተመክሮዎችን ቀምረን ወደ ተግባር ለመቀየር ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።
ዶ/ር ደረጀ ክፍሌ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት በበኩላቸው የመድረኩ ዋና አላማ ዶ/ር ችሮታው ይዘውት የመጡትን የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎችን ተሞክሮ ከሀገራችን እና ተቋማችን ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ስለምንተገብርበት ሁኔታ ለመወያየት ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በዲላ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመውን የምርምር መምሪያና ደንብ አርቃቂ ኮሚቴ ስራ ለመገምገም እንደሆነም ገልጸዋል። አያይዘውም ልምዳቸውን ለመድረኩ ላካፈሉት ዶ/ር ችሮታው አየለ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት እና የምርምር መምሪያና ደንብ አርቃቂ ኮሚቴዎችን አመስግነዋል።
ዶ/ር ሀብታሙ ተመስገን የዲላ ዩኒቨርስቲ ምርምርና ስርጸት ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር በበኩላቸው በዩኒቨርስቲው አስር ዓመት እስትራቴጂክ ዕቅድ መሰረት ምርምር ዘርፉን ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመስራት እና ፋይናንስ ድጋፍ አፈላልጎ ማግኘት እንዲሁም የተገኘው ድጋፍ የአስተዳደር ስርዓት ማበጀት ያለመ ውይይት መሆኑን አውስተዋል ።
ዳይሬክተሩ አክለውም የምርምር እና ተያያዥ ጉዳዮችን በጥብቅ ሕግና መምሪያ ለመስራት በማሰብ ኮሚቴ በመቋቋም በአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ያሉ ልምድና ተመክሮዎችን አጥንቶ መነሻ ረቂቅ ሀሳብ እንዲያቀርብ በተሰጠው ሀላፊነት መሰረት ለሁለተኛ ዙር መድረክ በማዘጋጀት ውይይት ተደርጓል ብለዋል።
በቀጣይ ተመሳሳይ መድረክ ተዘጋጅቶ ውይይት ከተደረገበት በዃላ በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ካውንስል ጉባኤ ተገምግሞ አስፈላጊ ሂደቶች አልፎ በዩኒቨርሲቲው ሰኔት እንደሚጸድቅ ዶክተር ሀብታሙ ገልጿል ።
በውይይት መድረኩ የተሳተፉት ዶ/ር ንጋቱ ኢብሳ በሰጡት አስተያየት መሰል የውይይት መድረኮች ለመምህራን እና ተመራማሪዎች መነቃቃትን ስለሚፈጥር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በውይይት መድረኩ የዩኒቨርስቲው አመራሮች፣ ተመራማሪዎች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞች እንዲሁም ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።