በዲላ ዩኒቨርሲቲ በገቢ ግብር አዋጅ እና መመሪያዎች ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ስልጠና ተሰጠ።

ዲ.ዩ የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም (ህ.ግ) የኢፌዲሪ ገቢዎች ሚኒስቴር ሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በዲላ ዩኒቨርሲቲ ለሚገኙ የግዢ ፣ የፋይናንስና የውስጥ ኦዲት ባለሙያዎች በግዢ ግብር አዋጅ እና መመሪያዎች ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ስልጠና ተሰጠ።
ሁለቱም የመንግስት ተቋም እንደመሆናቸው መጠን ይበልጥ ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው የተናገሩት በገቢዎች ሚኒስቴር ሀዋሳ ቅርንጫፍ የታክስ ስርዓት ዘርፍ ም/ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ታደሰ ስልጠናው በዋናነት በዩኒቨርሲቲው ሦስቱም ካምፓሶች ለሚገኙ የግዢ ፣ የፋይናንስ እና የውስጥ ኦዲት ባለሙያዎች ስለታክስ እና ስለ ገቢ ግብር አሰባሰብ መሠረታዊ ዕውቀት ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀ ስልጠና እንደሆነ ገልጸው ዩኒቨርሲቲው ሰፊ ተቋም እንደመሆኑ መጠን በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰራተኞች ደሞዝ ስለሚከፍልና የተለያዩ ግዢዎችንም ስለሚፈጽም ከዛ ጋር ተያይዞ የሚሰበሰቡ ግብሮች በወቅቱ ለመንግስት ገቢ እንዲደረግ የአሰራር ደንቦችንና መመሪያዎች ለባለሙያዎች ማሳወቅ ተገቢ ስለሆነ ስልጠናውን በዩኒቨርሲቲው ሊያዘጋጁ እንደቻሉ ተናግረዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፋይናንስና በጀት ዳይሬክተር አቶ ታምራት ታደሰ በበኩላቸው የመንግስትን ግብር በታማኝነት ሰብስበው ከሚያስገቡ ተቋማት መካከል ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ በመሆናቸው በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ከግብር አሰባሰብ ጋር ተያይዞ ስላሉ ህጎችና መመሪያዎች በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ስለሚገባ ስልጠናውን ለባለሙያዎች መሰጠቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ታምራት አክለውም መንግስት ባወጣው መመሪያና ደንብ መሠረት አጠቃላይ የመንግስት ገቢ በትክክል እየተሰበሰበ ገቢ እንዲሆን ሦስቱ ክፍሎች ተመጋጋቢ ሥራ የሚሰሩ በመሆናቸው ከገቢ ግብር አስራር ጋር ተያይዞ የሚመጡ ተጠያቂነቶች በቀጥታ ባለሙያዎች ላይ የሚወድቅ በመሆኑ ይህ ስልጠና መዘጋጀቱ ለባለሙያዎችም ይሁን ለክፍሉ ኃላፊዎች የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
የዲላ ታክስ ማዕከል አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ ዳግማዊት ጥሩነህ በበኩላቸው ስልጠናው የመንግስትን ገቢ በትክክል ከመሰብሰብ አኳያ ያለውን መመሪያና አዋጅ ለባለሙያዎቹ ሰፊ ግንዛቤ የሰጠ ስልጠና እንደነበር ተናግረዋል።