የዲላ ዩኒቨርሲቲ 16ተኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በፓናል ወይይትና በተለያዩ መርሃ ግብሮች በታላቅ ድምቀት አከበረ፡፡

ዲ.ዩ. ህዳር 29/2014 ዓ.ም. (ህ.ግ.) ህገ-መንግሰቱ የፀደቀበት ቀን የብ/ብ/ህ ቀን ሆኖ ተሰይሞ በየአመቱ እንዲከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሚያዝያ 21 ቀን 1998 ዓ.ም. መወሰኑን የተናገሩት ዶ/ር ችሮታው አየለ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዝዳንት 'ወንድማማችነት ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነት' በሚል መሪ ቃል ዘንድሮ የሚከበረው 16ተኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ልዩ የሚያደርገው ሀገር በህልውና ጦርነት ውስጥ ባለችበት ወቅት መሆኑና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የራሳቸውን ፍላጎትና የምዕራባዊያንን ተልዕኮ ለማሳካት ከተሰለፉ ጎራዎች ጋር የሚደረግ ጦርነት ላይ ባለንበት ወቅት መሆኑ ነው ብለዋል፡፡
እኛ ኢትዮጰያዊያን የዘመናት ታሪክ ባለቤቶች ብቻ ሳንሆን የዘመን ተሻጋሪ ድሎች ባለቤቶች መሆናችንን ያስታወሱት ዶክተር ችሮታው ዛሬ በአሸባሪው የህወሐት ቡድን የተደቀነብንን የሀገር ህልውና ፈተና ልክ እንደ ታሪካችን በመላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተባበረ ተሳትፎ ድል ለመንሳት ጫፍ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡
የፓናል ውይይት ጽሑፍ ያቀረቡት ዶ/ር ዳዊት ሀዬሶ የአስ/ተማ/አገ/ምክ/ፕሬዚዳንት እና መ/ር ኃይለማርያም ማሞ የሀገር ህልውና በማስከበር የኢትዮጰያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባበረከቱት ሚና እና ሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራላዊ ስርዓት ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ግንባታ ባለው አሰተዋጽኦ ላይ ትኩረት በማድረግ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ከተሳታፊዎችም ሀሳብና አሰተያየት ተሰጥቶበታል፡፡
ከተሳታፊዎች መካከል ዶክተር ዋቅሹማ ያደሳ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንሰ ኮሌጅ ዲን በበኩላቸው ባለፉት 27 ዓመታት ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ሀገሪን ይመራ የነበረው ህወሐት በህብረተሰብ ላይ ትልቅ ጫና እንዳደረሰ ተናግረው ያወጣውን ህገ መንግስት ከመተግበር አኳያ ከፍተኛ ክፍተት እንደነበረበት ተናግረዋል፡፡
በወቅቱም በውይይቱ ተሳታፊዎች 'ደሜን ለመከላከያ ሠራዊቴ' በማለት የደም ልገሳ የተደረገ ሲሆን ሁሉም ተሳታፊዎች ሀገር የምትጠይቀውን ሁሉ ለመስጠትና በተለያዩ ግንባሮች ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡