በዲላ ዩኒቨርሲቲ የዲጂታል መሰረተ ትምህርት የአጭር ጊዜ ስልጠና እየተሰጠ ነው

ዲዩ፤ ነሐሴ 9 ቀን 2011 ዓ.ም (ህዝብ ግንኙነት) የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ከኮምፒውቲንግ እና እንፎርማቲክስ ትምህርት ቤት ጋር በመተባበር ሁለት ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች መሠረታዊ የኮምፒውተር ትምህርት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
የኮምፒውተር መሠረታዊ ዕውቀት(Computer Basics)፣ የበይነ መረብ አገልግሎቶች አጠቃቀም (The Internet, cloud services and world wide web)፣ የአገልግሎት ሰጪ መተግበሪያ ፕሮግራሞች አጠቃቀም(Productivity Programmes)፣ የዲጂታል አኗኗር (Digital lifestyles)፣ የግል መረጃ ደህንነት አጠባበቅ(Computer security and privacy) በዲጂታል መሠረተ ትምህርት (Digital Literacy) ስልጠና እየተዳሰሱ ያሉ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው፡፡


ስልጠናው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በ3ኛው ዙር አንድ መቶ ቀናት ከ50 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የኮምፒውተር መሰረታዊ ስልጠና ለመስጠት የያዘው ዕቅድ አካል መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ፊልጶስ ተናግረዋል፡፡
በዚህ የማህበረሰብ አገልግሎት የኮምፒውተር ዕውቀት የሌላቸው ጀማሪ ተማሪዎች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች፣ ነጋዴዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ቴክኖሎጂን ተላምደው ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉና ኑሯቸውንም ለማቅለል መሠረታዊ ስልጠናው ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ 
ዳይሬክቶሬቱ ከአሁን በፊትም ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መሠረታዊ የኮምፒውተር ስልጠናዎችን በነፃ ሲሰጥ መቆየቱን ያወሱት አቶ ተመስገን ከፍተኛ ስልጠናዎችን ለመምህራንና ተማሪዎች በአነስተኛ ክፍያ ይሰጣል፤ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የማህበረሰቡ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴና የዕለት ተዕለት ክዋኔ ሁሉ ከቴክኖሎጂ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ የተሠጣቸው ስልጠና ለስኬት ቁልፍ በመሆን ውጤታማ እንዲንሆን ያግዘናል ብለዋል የስልጠናው ተሳታፊዎች፡፡